Quantcast
Channel: Kalkidan Amharic – Kal Tube
Viewing all articles
Browse latest Browse all 212

ሀምሳ አመት በህይወት!?-(ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

$
0
0

.hd
አንድ ጊዜ ከማስተምርበት የትምህርት ክፍል ውጭ ላሉ ተማሪዎች፣ በእንግድነት ተጋብዤ ስለግጥም አረዳድ (poetic interpretation) ገለጻ አድርጌ ነበር፡፡ ታዲያ ከንግግሬ መጨረሻ በተደረገው ውይይት አንዲት ተማሪ፣ ‹‹እስከሶስተኛ ዲግሪ ተምረሀል፤ ገጣሚ ነህ፤ አጫጭር ልቦለዶችንም አሳትመሀል፤ በጋዜጣም ታወጣቸው በነበሩ ጽኁፎች ብዙ አንባቢ ነበረህ፤ ቤተሰብ መስርተህ ልጆች ወልደሀል፤ . . . ከነዚህ ሁሉ አንተ ተሳክቶልኛል የምትለው የትኛውን ነው?›› ብላ እግረመንገዷን ጠየቀችኝ፡፡ በአጭሩ፣ ‹‹በሁሉም ተሳክቶልኛል ብዬ አላውቅም፤ ተሳክቶልኛል የሚል ስሜትም አይሰማኝም፡፡ እኔ ተሳክቶልኛል የምለው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ በህይወት መኖሬ!›› ብዬ መልሼላት ነበር፡፡
.
ታዲያ በቀደም በእለተጥምቀት፣ ሀምሳኛ የልደት ቀኔ ሲውል፣ ያ ሀሳብ ዳግም በህሊናዬ ገባ፡፡ እውነት በእኔ ዘመን ተፈጥሮ፣ እንደኢትዮጵያ ባለ ሀገር፣ ሀምሳ አመት በህይወት ከመቆየት የበለጠ ታላቅ ስኬት ምን አለ!? በእኔ ዘመን ሲያተኩስህና ሲያቃዥህ፣ ‹‹ቡዳ በልቶሀል›› ተብለህ ስራስር ስትጣጠን፣ ወይም ባልገሀል ተብለህ በርበሬ ስትታጠን፣ ገና በልጅነትህ ልትሞት ትችላለህ፡፡ ካልቀናህ ደግሞ ገና ለበርበሬ መታጠን ሳትደርስ እናትህ በጀርባዋ አዝላህ እንጀራ ስትጋግር በአናትህ ምጣዱ ላይ ልትተከል ትችላለህ፡፡ ብሎልህ ትምህርት ቤት ከገባህ ረዥም መንገድ በእግርህ ስትመላለስ እባብ ሊነድፍህ ይችላል፡፡ ስትዋኝ ደራሽ ውሀ ይጠርግሀል፤ ለፍሬ ለቀማ የወጣህበት ዛፍ ቅርንጫፍ ይገነጠልና ከስሩ ካለ አለት ላይ ትከሰከሳለህ፤ ወይም ገደል ትገባለህ. . . በእኔ ዘመን በልጅነት ለመቀጨት ሰበቡ ብዙ ነበር፡፡
.
ከዚህ ሁሉ አምልጠህ ሁለተኛ ደረጃ ከጨረስክ፣ ማትሪክ አላለፍኩም ብለህ እራስህን ልትሰቅል ትችላለህ፡፡ ማትሪክ ብታልፍ እንኳን ለኮሌጅ እየተዘጋጀህ እንደእኔ በብሄራዊ ውትድርና ልትታፈስ ትችላለህ፡፡ ለብሄራዊ ውትድርና ከታፈስክ ደግሞ ከማሰልጠኛ ስትጠፋ እንደነውሂብ አንበሳ ሲበላህ ይችላል፡፡ ይሁን ብለህ ስልጠናውን ከተጋፈጥክ ደግሞ እንደያሌ ያማ በስልጠና ወቅት ልትሞት ትችላለህ፡፡ ስልጠናውን ከጨረስክ የምትሄደው ከሻእብያ ወይም ከወያኔ ጋር ለመዋጋት ነው፤ ጦርነት ስትሄድ ደግሞ የሞት ድግስ ተጋብዘህ ሄድክ ማለት ነው፡፡
.
በብሄራዊ ውትድርና አለመታፈስም የመሞቻ መንገድህን አይቀንስልህም፡፡ ልብ በል! ያለኸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ እንደ ደርግ ያለው መንግስት ሀሳቤን ተቃወምክ ብሎ ገድሎ መንገድ ላይ ይጥልሀል፤ እንደ ኢህአዴግ ያለው መንግስት ደግሞ ገድሎ አሸባሪ፣ ጸረሰላም ይልሀል፡፡
.
በየጎዳናው የሚገድልህ መንግስት ብቻ እንዳይመስልህ፣ ከጥይት የሚያስፈራ፣ ከጥይት በላይ የሚገድል መኪና አለልህ፡፡ አሰፋ መዝገቡ፣ ‹‹በዚህ ሳምንት የሞት አደጋው ቀንሷል፤ የሞተው አስራአንድ ሰው ብቻ ነው›› እያለ በሚዘግብበት አዲስ አበባ እየኖርክ፣ ጠዋት ይዘሀት የወጣሀትን ትንፋሽ ማታ ይዘህ መግባትህ እንደምን አያስደንቅም!? . . . . እውነቴን ነው! በዚህ ባለንበት ዘመን ፕሮጀክት ነድፎ፣ ስፖንሰር አግኝቶ እንኳን ሀምሳ አመት መኖር ከተቻለ ታላቅ ስኬት ነው፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 212