Quantcast
Channel: Kalkidan Amharic – Kal Tube
Viewing all articles
Browse latest Browse all 212

አርዕስት አልባ ሀተታ-(ቻላቸው ታደሰ)

$
0
0

የሚከተለውን ዲስኩር የከተብኩት በአጋጣሚ ተወዳጅ የኪነጥበብ ሰው የሆነውን የመኮንን ላዕከን ቀልድ-አዘል አነጋገር ዘይቤ ካሰብኩ በኋላ ነው፡፡
የቀልድ ዕጦት
በእውነት ማህበረሰባችን በቀልድ ዕጦት (humor deficit) ስቃይ ላይ ነው፡፡ በቋንቋዎቻችን ውስጥ ቀልዶች/ተረቦች ቢኖሩም በራሳችን መቀለድ ግን አልለመድንም፣ በርካቶቻችን ሰው እንኳ ለአንድ አፍታ ሲቀልድብን/ሲተርበን የ“ሞት ሽረት” ነገር እናደርገዋለን፤ እንደ ገዥዎቻችን “በመቃብሬ ላይ!” እንላለን፡፡ ቢያንስ በአደባባይ በፖለቲካችንና በመሪዎቻችን አንቀልድም (ይህንን ሁኔታ ግን ሁሌም በጨቋኝ አገዛዞችና ማሳበብ የሚያስኬድ አይመስለኝም፤ ራሳችን ካልዋሸን በስተቀር እስካሁን ቀልዶ የታሰረ አላየንም)፡፡ መሪዎቻችንም በራሳቸው ወይም ያልመረጣቸው ህዝብ ለእነሱ ባለው አተያይ ላይ አይቀልዱም፤ የሃይማኖት አባቶችና ተቋማትማ ቀልድን ጭራሹን ውግዝ/ሃራም ያደረጉት ይመስላሉ፡፡ ያለ ማህበረ-ፖለቲካ ቀመስ ቀልድ ሀገራችን ወና ምድረ በዳ (barren land) ትሆንብኛለች፡፡ በቁስ ሃብት ብቻ በልፅገው በመንፈስ የደኸዩ እያልን በምንተቻቸው ሀገሮች ያሉ ፖለቲከኞች ቀልድ ነፍሳቸው እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ማህበረ-ፖለቲካ ቀመስ ቀልድ አልባ የሆነ ማህበረሰብ የሞተሩ ቡለኖች ሻክረው ጉዞው እንደሚገታበት አስባለሁ፡፡ ቀልድ የገነተሩ ቡለኖችን አለስላሸ ቅባት (lubricant) እንደሆነ አድርጌ አየዋለሁ፤ ከጅምላ ድብታ የሚያነቃ ተፈጥሯዊ ቅመም፡፡ (ብዙዎቻችን ድብታ ውስጥ ስለሆንን አይታወቀን ይሆና እንጂ ማህበረሰባችን በድብታ መዋጡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡)
ፖለቲካ ባህል እንደ ሸክም
ፖለቲካችን በአስፈሪ ሁኔታ ደረቅ ነው፤ የፖለቲካ ባህላችንን እንኳ ነጥለን ብናየው ግትር (rigid) መስመሮች የተሰመሩበት ነው፤ ብዙ ወለፈንዶችን (absurdities) እና ተቃርኖዎችን (paradoxes) ያዘለ ነው፡፡ በእርግጥ ቅራኔ በራሱ መጥፎ አይደለም፤ በአሮጌው ፋንታ አዲስ ባህል እንዲጎመራ የሚያደርገው ቅራኔ ነውና፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ያዘለው “ቅራኔ” ግን ገና ወደ “ግጭት” (clash) ደረጃ ስላላደገ በባህላችንም ሆነ በፖለቲካችን የ“thesis-antithesis-synthesis ዑደት አልታየበትም፡፡ የ“thesis-antithesis-synthesis ዑደት ህልዮት አባት የሆነው ጀርመናዊው አንሰላሳይ ሄግል በthesis (ነባራዊ ሁኔታ) ውስጥ በሚፈጠር ተቃርኖ ሳቢያ ነባራዊ ሁኔታውን የሚገዳደረውን ተፃራሪ ሁኔታ (antithesis) ይለዋል፡፡ የthesis እና antithesis ግጭት ሲጧጧፍ በthesis መቃብር ላይ በዓይነቱ የተለየ አዲስ ነባራዊ ሁኔታ (synthesis) ይወለዳል፡፡ አዲሱ synthesis በፋንታው ሙሉ የበላይነቱን ሲጎናፀፍ ገዥ thesis ይሆንና በሂደት ደግሞ ሌላ ተገዳዳሪ antithesisን ለመጋፈጥ ይገደዳል፡፡ የእኛ ፖለቲካ ባህል ግን ባለበት እንደተቸከለ አለ፡፡
መድሃኒታችን እምብዛም የማይነገርት “የፖለቲካ ባህል” (political culture) ለውጥ ነው፡፡ የፖለቲካ ባህል ሽግግር ግን የፖለቲካ አብዮት እንደማካሄድ ቀላል አይደለም፡፡ ገዥዎቻችንን ጨምሮ ሁሉም የስልጣን ምንጭ የሆኑ ተቋማት የተገነቡበት መሰረት ጨቋኝ (authoritarian) ነው፤ ከላይ ወደታች የሚወርድ (hierarchical) እና አባታዊ (patriarchal) ነው፡፡ እነዚህ ባህሪያት በሌሎች ሀገሮች ቢታዩም የእኛ ግን ልኬት አልባ ነው፡፡ ገዥዎቻችንም የዚሁ ፖለቲካ ባህል ውጤቶችአድርጎ በማየት ፋንታ ጭራሹን ከማህበረሰቡ ስነልቦና የተነጠሉ፣ ከጠረፍ ማዶ የመጡ ልዩ ፍጡራን አድረግን በመውሰድ ራሳችንን በማታለል ተክነንበታል፡፡ እንደ ሬት እየመረረንም ቢሆን “A people gets a government it deserves” (ማንኛውም ህዝብ የሚያገኘው የሚገባውን (ቃሉ ይጠብቃል!) መንግስት ነው) የሚለውን አባባል ደጋግመን ለመፈተሽ እንፈራለን፡፡ ይህ አባባል ሲነሳ የሚያኮርፉ ሰዎች በርካታ መሆናቸውን አላጣሁትም፤ ያው በቀናዒ ሃሳብ ላይም ቢሆን ማመፅ/ማኩረፍ ባህላችን ነው፡፡
እንደ ህዝብ ሁለንተናዊ ውስጣዊ ፍተሻ (soul-searching) ለማካሄድ ዳተኞች ነን፡፡ የተወሰነውን የተጠያቂነት ሸክም ድርሻ ለመቀበል ካልተዘጋጀን በድህረ-ኢህአዴግ ዘመንም ነፃነትን ጥቂቶች ቢያምጧት እንጂ ብዙሃኑ ላይወልዷት ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ካልተለወጠ በመንግስት ለውጥ ማግስት የነፃነት ጮራ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ቦግ ብሎ ይበራል ብለው የሚያምኑ ተስፈኞች (የፖለቲካ ልሂቃንን ጨምሮ) ህልም ቅዥት ብቻ ይሆናል፡፡ ጭቆናን ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ የሚቀበል ባህል ገና እንደደረጀ አለ፡፡ በብዙዎቻችን በተለይ በ“ለውጥ ናፋቂ” ፖለቲካ ልሂቃን አዕምሮ ውስጥ እንደ እሾክ ተሰንቅሯል፡፡ እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራንድ ራስል “We have, in fact, two kinds of morality side by side: one which we preach but do not practice, and another which we practice but seldom preach” ያለውን እሰኪ ደጋግመን እናጢነው፡፡ የቱ ጋ ነን?
ምን ይሻለናል?
የፖለቲካ ባህልን መቀየር የሚችሉት የትምህርት ስርዓት/ትምህርት ቤቶች፣ ሲቪል ማህበረሰብና ሜዲያ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳልሆኑ መስማማት አለብን፡፡ ለሀገራችን ህመም (predicament) ከፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻውን ፍቱን ፈውስ መጠበቅ ሞኛሞኝነት (naivety) ነው፡፡ የትኛውም ነፃነቱን የተጎናፀፈ ህዝብ ነፃና ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ፖለቲካ ባህሉን በትምህርት፣ ሜዲያና ሲቪል ማህበረሰብ እየታገዘ ራሱ በሂደት ቀረፀው እንጂ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጓዳ አልተቸረውም፡፡ እንቆቅልሹ ግን ሜዲያችንም ሆነ የትምህርት ስርዓታችን የኋላቀሩ ፖለቲካ ባህል ሰለባ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ባህሉ እንዲቀጥልም (perpetuate እንዲያደርግ) ከማገዝ ገና አልተላቀቁም፡፡
ኪነጥበብንም የኋላቀሩ ፖለቲካዊ ባህል ታጋች (hostage) ነው፡፡ በበኩሌ የበዕውቀቱ ስዩም ስነፅሁፋዊ ነፃነት አድናቂ የሆንኩት ለዚህ ነው፡፡ ከበዕውቀቱ አዕምሮ ብቻ በተወለደው ነፃነት እንኳን ስነፅሁፍ ምን ያህል ሃሴት ለማየት እያጣጣረች እንደሆነ ለማንም ስውር አይሆንም፡፡ በዕውቀቱ ሲፅፍ ገናናውንና ኋላቀሩን የፖለቲካ ባህል አሽቀንጥሮ ጥሎ ነው፡፡ ችግራችን ግን በዕውቀቱ ያሽቀነጠረውን ድሪቶ ሌላው እያነሳ ይለብሰዋል፤ ያጎነቆለችው የለውጥ ፍሬም እንደቀጨጨች ትቀራለች፡፡ ስነፅሁፍ ለነፃነታችን አይተኬ ሚና እንደሚኖረው አይካድም፡፡ የባለተውኔቱ፣ ገጣሚውና ደራሲው ቫስላቭ ሃቬል ስራዎች ኃያልነትና የሰውዬው የማይነጥፍ ነፃነት ናፋቂነት አዲሲቷን ቼክ ሪፐብሊክን ወደ ነፃነት ጎዳና በስኬት እንደመራት ልብ ይሏል፡፡ ቫስላቭም የመጀመሪያው ፕሬዝዳንቷ ሆኗል፡፡
በውጭ ሀገራትም እንደ አሸን የፈሉት የፖለቲካ ድርጅቶች እንጂ ኢመደበኛ የውይይት መድረኮች (informal dialogue forums) አይደሉም፡፡ ብዙ ሰው የሚመሰጠው “የኢትዮጵያ ትንሳዔ ምክክር መድረክ” (ልቦለድ ስያሜ ነው!) ምናምን በሚባሉ ኢመደበኛና ሁሉን ዓቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ ስብስቦች ሳይሆን በፖለቲካ ድርጅቶች መሆኑ ገና መከራችንን ያበዘዋል፡፡ ያልለዘቡ ቁስሎችን በዘላቂነት ማድረቅ የሚችሉት፣ ወደፊት ትንሳዔን የሚያጎናፅፉን ግን እነዚህ ስብስቦች እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊሆኑ አይችሉም፤ እነሱማ በተፈጥሯቸው በቁስል ላይ ጨው ነስናሽ ለመሆን የተጋለጡ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ልሂቃን መወለድ የነበረባቸው ከእነዚህ ኢመደበኛ ሲቪል ስብስቦች ማህፀን መሆን ሲገባው በእኛ ሁኔታ ግን ቅደም ተከተሉ ተዛብቷል፤ ከፈረሱ ጋሪው ቀድሟል፡፡ ሃምሳ ዓመት ሙሉ የፖለቲካ ልሂቃንና ድርጅቶች ጭንጋፍ እየሆኑብን የተቸገርነው በተፍጥሯዊው ማህፀን ዑደታቸውን ጠብቀው ስለማይወለዱ አይደለምን? ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችንና ልሂቃንን የሚተች ሰው ብቅ ካለ ፖለቲካ ባህላችን ሰይፉን ይመዛል፤ እንደ እባብ አናቱን ቀጥቅጦ ድራሹን ያጠፋዋል፡፡ ህዝቡ በራሱ ላይ የነገዎቹን አዲስ ጨቋኞች ይሞሽራል፡፡
ግልፅ ጥሪ
ድንበር አልባዎቹን፣ ሁለገቦቹን ሲቪል ድርጅቶችን/ስብስቦችን/መድረኮችን እንውለድ! የህብረተሰብን ህመሞች የሚነካካ፣ ከኋላ ቀሩ ፖለቲካዊ ባህል ነፃ የወጣ ስነፅሁፍን እናበረታታ! ህዝብ፣ ሀገር ፀንቶ የሚቆመው በሲቪል ማህበረሰብ፣ በስነፅሁፍ፣ በሜዲያና ትምህርት ስርዓት ቅንጅት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በእነዚያ መድረኮች ተሞርደው ተስተካክለው እንዲፈጠሩ መተባበር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ወደፖለቲካ ድርጅቶች ካዝና የፈሰሰው ሙዓለ ንዋይ ለእነዚህ ድርጅቶች ደርሶ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ቢያንስ በማይናወጥ መሰረት ላይ እንሆን ነበር…
በመጨረሻም ለዚህ ዲስኩር/ሃተታ መነሻ የሆንከኝ መኮንን ላዕከ ሆይ! የጥበብ መንገድህን ሁሉ ፈጣሪ ቀና ያድርግልህ! ኪነጥበብ ራሱን ከእገታ ነፃ አውጥቶ ሀገርህንም ነፃነት የሚያጎናፅፍበትን ቀን ያቅርብልህ!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 212

Trending Articles