ፅሁፍ ዝግጅት – ዘመነ ምህረት (የቀድሞው መኢአድ ም/ፕሬዝደንት)
(አቶ አሸናፊ አካሉ አበራ ሀሳብን በማንሳት አግዞኛል)
ይህንን ፅሁፍ በአማራ ስም አማራውን ለሚያቆስለውና ለህወሓት ስሪት ለሆነው ብአዴን አመራሮችና አባላት ልፅፍ ስሰናዳ ለፅሁፉ መነሻ የሆኑት ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነሱም፡-
1ኛ. አቶ አለምነው መኮነን (የአብአዴን የህዝብ ግንኙነት) በ01/02/08 ዓ.ም በአማራ ክልል ቴሊቪዥን ስለ 35ኛው የብአዴን በዓል አከባበር የሰጠው መግለጫ፤
2ኛ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ጭቆና፣ በደሉን የሚሰማና አለሁ ባይ ተቆርቋ ተቋምም ሆነ መሪ አለመኖሩን ለማሳወቅ ነው፡፡
የጥንታዊና የመካከለኛውን ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ባለበት ትተን ከዘመናዊው ታሪክ ብንነሳ አብዛኛው ዘመን ገዥና የገዥ መደብ ሆኖ ኖሯል ተብሎ የሚወቀሰው የአማራ ህዝብ ነው፡፡ እገሌ የሚባለው መሪ የእገሌ ብሄር ተወላጅ እንጅ የገሌ አይደለም የሚባለው ዘር ቆጠራ ውስጥ ለመግባት አይደለም አነሳሴ፡፡ በዚህ ፅሁፍ በገዥና የገዥ መደብ ስም በአማራው ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው ሰቆቃ እና አማራውን ወክዬ ስታገል 35 አመት አስቆጥሬያለሁ የሚለው ብአዴን ህዝቡን እንደማይወክል ለመሞገት ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ትናንት ‹‹አማራ›› በተባሉ ገዥዎች፣ ዛሬ ደግሞ ‹‹አማራ ጨቆነን›› ባይ ባለጊዜዎች የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኗል፡፡ እየሆነም ይገኛል፡፡ አጤ ምኒልክ በኦሮሞና ደቡብ ፈፀሙት በተባለው ግፍ በአማራ ህዝብ ላይ ጣት ሲጠቆም፣ አጤ ዮሃንስ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላ ምላሳቸውን ስለቆረጧቸው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ትግራይን በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ አይሆንም? ዛሬ እነ ጃዋር ሞሃመድ፣ መኩሪያ ቡልቻ፣ መሃመድ ሀሰን፣ የተባሉት ‹‹ምሁር›› ነን ባዮች በሚፈሰው የዘውግ ፖለቲካ ተንሳፍፈው በሚነፉት ድስኩር በስመ አማራ ስንቱ ከቤት ንብረቱ ተፈናቀለ፡፡ ተሰደደ፡፡ ተገደለ፡፡ ለሆነው ሁሉ ጥናት ተደርጎ የሚጠየቅ አካል ቢኖር የብአዴን አመራሮች ወክለንሃል በምትሉት ህዝብ ላይ ስለደረሰውና ስላደረሳችሁት ሁሉ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች በሆናችሁ ነበር፡፡ ከእናንተ ህሊና አልባ ህይወት የእኛ በአካል መታሰር በስንት ጣዕሙ! በእርግጥ ታሪክ ፍርዱን መስጠቱ አይቀሬ ነው፡፡
ጅብ ከሄደ….
አቶ አለምነው መኮንን በቴሊቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የ35ኛ ዓመት በዓልን ማክበር ያስፈለገበትን ዓላማ ሲዘረዝሩ ለእሳቸው እኔ አፈርኩ፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
• የኢህዴንን ወደ ብአዴን መቀየር አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ
• የአማራ ህዝብ ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ያደረገውን አስተዋፅኦ ለወጣቱ ለማሳወቅ፣
• የአማራ ህዝብ ጨቋኝ አለመሆኑን ለማስገንዘብ
ይህን ባየሁ ጊዜ ታዲያ ‹‹እኒህ ሰውዬ ከጤናቸው ይሆኑ?›› የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ ‹‹የትምክት ለሃጩን ሳያራግፍ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ….›› ብለው በአማራው ላይ የተፉት ምራቅ ሳይደርቅ ምን የሚሉት መገልበጥ ነው ለአማራው ተቆርቋሪ መምሰል? የአማራው ህዝብ ጨቋኝ አለመሆኑን ለማስገንዘብ ስትሉስ ጨቋኝ እየተባለ ይህን ያህል ጊዜ ፍዳውን ሲያይ፣ ሲረገጥና ሲሰቃይ የት ነበራችሁ? ጨቋኝ ላለመሆኑ ጥናት እያጠናችሁ? እነ በረከት ‹‹የአማራን ትምክት እናስታግሳለን›› ሲሉ የት ነበራችሁ? የአማራ ህዝብ ለአንድነት ያደረገው ተጋድሎስ የሚጀምረው ከ35ኛ በዓላችሁ በኋላ ይሆን?
በደል ለበዳዩ ምኑ ነው?
የብአዴን አባላት ሆይ! ወክለንሃል እያላችሁ የምትገድሉትና የምታስገድሉት፣ የምትጨቁኑትና የምታስጠቁት፣ የአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው ሁሉ ባይሰማችሁ አይገርምም፡፡ እናንተ የበዳዩ እንጅ የተበዳዩ፣ የጭቁኑ፣ የመከረኛው ህዝብ አካል አይደላችሁምና፡፡ በምቾትና በድሎት ችላ ብትሉትም እራሳችሁ የምታውቁትን የህዝብ በደል ላስታውሳችሁ፡፡
• ‹‹ኤርትራ/ትግራይ በገዥው የአማራ ህዝብ ቅኝ ግዛት ተይዟል›› የሚለውን የሻዕቢያንና የወያኔን ማንፌስቶዎች ተቀብላችሁ፣ አብራችሁ ለመስራት አልተስማማችሁም? ይህስ የዛሬው ፕሮፖጋንዳችሁ ጋር ሙሉ በሙሉ አይጣረስም?
• ኢህዴን ወደ ብአዴን ተቀይሮ የአማራ ህዝብ ወኪል መስሎ ሲቀርብ የትኛው የአማራ ተወላጅ ይሆን መሪ የሆነው? በረከት ስምኦን? ተፈራ ዋልዋ?….. ጀኔራል ኃይሌ ጥላሁን ጥርስ ተነክሶበት እንዲጉላላ የተደረገው በብአዴን ስብሰባ ላይ ‹‹ብአዴን ውስጥ የአማራ ተወላጅ የለም›› ብሎ በመናገሩ አልነበረም? በ1987 ዓ.ም ማርቆስ ላይ በተደረገው ስብሰባ ስንቱን የአማራ ተወላጅ ለህዝብ ይቆማል ተብሎ ከብአዴን አላባረራችሁም? ስለ ሙሉዓለም አበበ ግድያስ ምን እየተባለ ይሆን?
• ያለ ህዝብ ፈቃድ የወልቃይትና ሁመራ መሬት ከጎንደር፣ አላማጣ፣ ራያ ቆሞ፣ ኮረም፣ ከወሎ በመንጠቅ ለህወሓት ለመስጠት ሲወሰን፣ አብዛኛዎቻችሁ እሺ ብላችሁ አልተቀበላችሁም? የተላከላችሁን ውሳኔስ አላፀደቃችሁም?
• ጓንግና ጓንግ ባሻገርን፣ ኮር ሁመራን፣ ወደቁራን፣ ገላሎባን፣ ስፋዋን፣ ባህረ ሰላምን፣ መተማን፣ ቋራ ከቁጥር 1-8 እና ነብስ ገበያን ለሱዳን የሰጣችሁት ለአማራ ህዝብ ስለምትታገሉ ነው? በእናንተ ‹‹ጥረት›› ነገ ታሪክ መፅሃፍ ላይ የአጤ ቴዎድሮስ የትውልድ ቦታ ሱዳን ልታደርጉት ነው፡፡
• የአማራ ክልል ብቻ ተለይቶ በ1987 ዓ.ም አርሶ አደሩ በሙሉ በነፍስ ወከፍ የያዘውን መሳሪያ እንዲቀማ የተደረገው በሌሎች ክልሎች የተያዘው መሳሪያ ስለማይተኮስ ወይንስ አማራ በኢትዮጵያ ስጋት ስለሆነ ራቁቱን መቅረት አለበት ብላችሁ ስለምታምኑ?
• በ1989 ዓ.ም በአማራ ክልል በተካሄደው የመሬት ‹‹ሽግሽግ›› ቢሮክራትና ቅሬተ ፊውዳል በሚል ፍረጃ ብዙሃን መሬቱ ሲነጠቅ፣ በድህነት እንዲማቅቅም ሲደረግ፣ ያኔ ነጭ ለባሽ የነበረው የጎጃም ህዝብ ያቀረበው ቅሬታ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቀባይነት ቢያጣ ‹‹ጎጃም አዘነ›› የሚል ቅፅል የወጣለትን ልብስ መልበስ የጀመረው በእናንተው ዘመን አይደለም? ይህ ህዝብ መሬቱ ተነጥቆ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት ደርግ ይገዛ የነበረው አማራን ብቻ ስነበር ይሆን?
• አይናችሁ እያየ ንብረቶች ወደ ትግራይ አልተጋዙም? ሌላው ይቅር፤ ጣሊያን የሰጠውና ጎንደር ላይ ሀይል እንዳይቋረጥ ያግዝ የነበረው ግዙፍ ጀኔሬተር ተነቅሎ ሲወሰድ የት ነበራችሁ? ደርግ ለቴክኒሻኖች ማስተማሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ ዘመናዊ ማሽኖች፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙ የነበሩ ሜሪኩሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ወደ ትግራይ የተጓዙት እናንተ ‹‹የአማራ ወኪል ነን›› ባላችሁበት ወቅት አይደለም? አፈር ሳይቀር እንደተጫነ የማታውቁ ሆናችሁ ነው?
• የአማራ ተወላጅ ሴቶች መሃን የሚያደርግ ክትባት ሲሰጣቸው፣ ዘር ማጥፋት አንዱ አካል መሆኑን ከእናንተ የተደበቀ ነገር ኖሮ ነው?
• የምታመልኩት ህወሓት መራሽ መንግስት ነፍጥ አንጋቢዎቹ ሳንጃ፣ ጎርቢጥ ላይ የ14 ሰዎችን ደም ካፈሰሰ በኋላ ከግድያው ያመለጡ ሰዎች በምሬት የአርበኞች ግንባርን መመስረታቸው ለእናንተ ይጠፋችኋል? ምን አልባት በድሎት ከዘነጋችሁት በወቅቱ የአርማጭሆ አስተዳደርና በ2004 ዓ.ም የጎንደር ከተማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊን ጠይቁት፡፡ አስከሬናቸው ሳይቀበር ውሻ እንዲበላው ነበር የተደረገው፡፡
• በወቅቱ በምስራቅ አፍሪካ ከነበሩት ሁለት የቀዶ ጥገና ሀኪሞች አንዱ በኢህአዴግ እስር ቤት ማቅቀው የሞቱት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ጠንካራ የነበረው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት፣ አቶ አሰፋ ማሩን የመሰሉትን ምሁራን ማን ገደላቸው? ጭቆናን የተቃወሙ የአማራ ተወላጅ ምሁራን ሲሰደዱ፣ ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ እናንተ የት ነበራችሁ?
• በ1997 መለስ ዜናዊ ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ የአማራ ክልል የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ድሆችና መንገድ ላይ የወደቁት በሽተኞች ከባህርዳር ከተማ ተለቅመው፣ በመኪና ተጭነው የት እንደተጣሉ አታውቁም?
• ‹‹አማራ ጨፍጫፊ›› ነው በማለት ለዚሁ ቂም መፈልፈያ ይሆን ዘንድ የሲዳማ ባህል አዳራሽ፣ የአኖሌ ሀውልት ማቆም፣ በስርዓተ ትምህርት ደረጃም መቅረፅ፣ ማሰልጠኛ ማንዋል አዘጋጅቶ ጥላቻን በስልጠና መልክ መስጠት ምን የሚሉት ቢሂል ነው? በተለይ ተወካይ ነን ለምትሉት! እንደለመዳችሁት ‹‹አናውቅም!›› እንዳትሉ ደግሞ ስልጠናውን የሚሰጡት እነ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ በረከት ስምኦንና ፣……ሌሎችም አመራሮቻችሁ ናቸው፡፡
• በአርባጉጉ፣ በቴፒ፣ በጅማ፣ በበደኖ፣ በጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉል እና በጋምቤላ አማራ በመሆናቸው ብቻ የተፈናቀሉት፣የተገደሉት፣ ‹‹ሀገራችሁን ግቡ›› የተባሉት፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ሀገር አገኛችሁላቸው?
• የህዝቡን አንድነት ለማዳከም አብሮ የኖረውን የቅማንት፣ የአገው… ከፋፍላችሁታል፡፡ የቅማንት ማህበረሰብም በጣና አካባቢ የራሱ ግዛት እንዲኖረው እየሰራችሁ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ሴራችሁ የአማራ ህዝብ ወኪል ስለሆናችሁ ነው?
• የተለያዩ ፖሊሲዎች ሲሞከሩ የአማራ ህዝብ እንደ አይጥ መሞከሪያ ይሆናል፡፡ ‹‹ምርጥ ዘር››ም ሆነ የትምህርት ፖሊሲ (ስምንተኛ ክፍል ድረስ በአማርኛ) የሞከራችሁት የት ነበር? አብዛኛዎቹን ፖሊሲዎች በአማራ ላይ ሞክራችሁ አይደለም ድክመታቸውን ተለካ የተባለው?
• የንግድ ተቋማት፣ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች፣ በማን እጅ እንደሆኑ እናንተ አጥታችሁት ይሆን? ይህንን ለማወቅ ጎንደርን ብቻ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ ካፍቴሪያዎች፣ ሱቆች፣ ሆቴሎች፣ ህንጻዎች.. የሚተዳደሩት በህወሓት ደጋፊዎችና አባላት አይደለም? በአርማጭሆ፣ ቋራና መተማ ለም መሬቶች በህወሓት ቁጥጥር ስል አይደሉም? በክልሉ የጉምሩክ ቢሮ ቀዳሚዎቹ የስልጣን ቦታዎች ለማን የተተው ናቸው? ለዋቢነት ከ2004 -2005 በጎንደር ከተማ ንግድ ፅ/ቤት በመለስና በምክትሉ አባዲ መካከል ‹‹ለምን ከ500 በላይ የትግራይ ተወላጆች የያዟቸው የንግድ ተቋማት ያለ ፈቃድ ይሰራሉ?›› በሚል የተነሳውን ግጭት መለስ ብላችሁ አስታውሱ፡፡
• ሱዳናውያን ድንበር እየጣሱ የሚያቀጥሉትና የሚዘርፉትን የህዝብ ንብረት ቸል ማለታችሁ ሳይበቃ፣ በ2007 ዓ.ም ከእንፍራንዝ ወደ ሮሮታ አሳፍርሻለሁ በሚል ኩላሊቷን አውጥቶ፣ ገድሎ በመጣል፣ ሊሰወር ሲል ሀሙሲት ላይ በህዝብ ርብርብ የተያዘውን ሱዳናዊ በመቶ ሺህ ብር ክፍያ ያውም ጥቃት እንዳይደርስበት በመከላከያ ታጅቦ እንዲወጣ ያደረጋችሁት ለአማራ ህዝብ ወኪል ስለሆናችሁ ነው? ይህን ድርጊት የተቃወሙትን ወጣቶች ያሰራችሁት ለማን ስለቆማችሁ ይሆን?
‹‹አሸባሪው›› አማራ
ዛሬ አማራ ማለት አሸባሪ ተብሎ ተፈርጇል፡፡ ከደህንነት ቢሮዎች እስከ ቂሊንጦ እስር ቤት፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ፣….. ድረስ ያለውን አማራ በመሆኑ ብቻ እየተሰቃየ ያለውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እኔ በምገኝበት ቂሊንጦ፣ ዞን አንድ ዘርዝሬ የማልዘልቀው (ወጣቱን ልተወውና) ለአቅመ አዳም ያልደረሱት ገብናናው ጨቅሌ፣ አብዩ ተስፋ፣ ጀጃው ኃይሌ፣ ዶክተሩ ባዬ እድሜያቸው ከ14 አመት የማይበልጡ ህፃናት ናቸው፡፡
የ‹‹የዘርህ ያንዘረዝርህ››ን ብሂል የሚከተሉት የወቅቱ ገዥዎች መሰሪያዎቻቸው ደህንነት ተብዬዎቹ ጎንደር ብልኮ አካባቢ ከሚገኘው የደህንነት ፅ/ቤት፣ ባህርዳር ኢሜግሬሽን (ደህንነት) ፅ/ቤት፣ እስከ አዲስ አበባው ማዕከላዊ የሚያደርሱት ግፍና በደል ላየው ይቅርና ለሰማው የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ አማራ መሆን ወንጀል፣ ሽብር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ‹‹የምኒልክ ዘር፣ ጥንብ አማራ፣ ወራዳ አማራ….›› እያሉ ጉድጓድ ላይ ጥለው ሽንት መሽናትና ምራቅ መትፋት፣ ራቁትን መግረፍ፣ ‹‹የትምክተኛው አማራ ዘር መጥፋት አለበት›› እያሉ ብልትን መቀጥቀጥ፣ ‹‹አማራን ሱሪውን አስወልቀነዋል፣ ሱሪህን አውልቅ›› እያሉ ማንገላታት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ተቋማት ውስጥ በአማራ ላይ የሚደርሱ የዕለት ተዕለት ግፎች ፀሃይ ወጥቶ የመግባትን ያህል ተለምደዋል፡፡ ‹‹መለስ ጀግና፣ ታማኝ በየነ እና አበበ ገላው ውሻ ናቸው በል›› እንዲሁም፣ ‹‹ትግርኛ ተናገር!›› በሚል የሚደርሰው ድብደባ፣ የሰዎቹን የውስጥ ጭንቅላት አሳይቶናል፡፡
ይህ ሁሉ ጉድ የሚደርሰው የመተማ ተወላጅ በሆነው ደርሶ አያል (ባህርዳር ላይ)፣ እና አሸናፊ (የጣቁሳ ተወላጅ) በሆኑት የብአዴን /የህወሓት ተለጣፊዎች እንዲሁም በትግርኛ ተናጋሪ ደህንነቶች ነው፡፡ ባህርዳር ላይ በብአዴንና በህወሓት ደህንነቶች አማራ በግፍ ሲረገጥ እዛው ቁጭ ብሎ የአማራ ተወካይ ነኝ ማለት በጣም ያሳዝናል፡፡ ስላቅም ነው፡፡
ብአዴን፡- ሰው በላው ድርጅት
ይህንን ፅሁፍ ሳዘጋጅ ሞኝነት ቢጤ እንደተሰማኝ አልክድም፡፡ ለራሱ አባል ያልሆነው ብአዴን እንዴት የህዝብን ጥቅም ሊያስከብር ይችላልና የሚል መጠይቅ ውስጥ በመግባቴ፡፡ እስኪ ሰው በላው ድርጅት የበላቸውን አባላት ላስታውሳችሁ፡-
• መላኩ ፈንታ፡- የቀድሞ ጉምሩክ ዳይሬክተር የህወሓት የበላይነት ላይ ጥያቄ በማንሳቱ ዛሬ መገኛው ቃሊቲ እስር ቤት ሆኗል
• ብ. ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ብ. ጀኔራል አለማየሁ፣ ኮሌኔል አሳምነው ፅጌ፣ በ2001 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ልትፈፅሙ አሲራችኋል በሚል እስር ቤት ይገኛሉ
• ሙሉ ዓለም አበበ፡- በ1987ቱ የማርቆስ የብአዴን ስብሰባን ተከትሎ አይደለም የተገደለው?
• ብርሃኑ፡- የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረውና በአማራው ላይ የሚደርሰውን በደል ዘግይቶ በመንቃቱ በፖሊስ አባላት ‹‹የት ነበርክ›› የሚል የቅፅል ስም የተሰጠው፣ የአልማ ፅ/ቤት የተቃጠለበትን ሁኔታን ሲያጣራ ግልፅ ባልሆነ መንገድ መገደሉን ዘነጋችሁት? በዚህ ጉዳይ እነ አቶ ህላዊ የሆነ ነገር ማለት ይገባቸዋል፡፡ ጠይቋቸው!
• ጀኔራል አበባው ታደሰ፡- አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ሳይታወቅ፣ በከተማ የቁም እስር ተገሎ እንደሚኖር አታውቁም ይሆን?
• ነባር የተባሉት ‹‹የብሄር ተዋፅኦ›› በሚል፣ ለምሳሌ ያህል በ2005-2006 ከሻንበል በላይ ያሉት የሰራዊት አባላት መመንጠራቸው ለእናንተ ድብቅ ሆኖ ነው?
• በቅርቡ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አጃቢ የነበረው ኢንስፔክተር አበበ የኋላ ሶስት ራሱን አሸባሪ ተብሎ ቂሊንጦ ተቀላቅሏል፡፡ የታሰረበት ምክንያት አቶ ገዱም ሆነ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ዘውዱ ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ የክልሉ መንግስት አጣርቶ ‹‹ችግር የለበትም›› ብሎ ሲፈታው በፌደራል ደህንነቶች ጫና ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ታስሯል፡፡ በወልቃይትና ጠገዴ፣ በትግራይና አማራ ክልል መካከል በታህሳስ 2007 ዓ.ም ተነስቶ በነበረው ግጭት ተሳትፏል በሚል በህወሓት ጥርስ ውስጥ መግባቱን ብዙዎቻችሁ ታውቃላችሁ፡፡
ብአዴን እንደ ጉፈላ ላም
ታዲያ ብአዴን ማን ነው? ማንንስ ወክሎ ነው? ብዬ ሳስብ የጉፈላ ላም ትዝ ትለኛለች፡፡ አንዲት ላም ወልዳ ጥጃዋ ከሞተባት ገበሬው የጥጃዋን ቆዳ ይገፍና ቆዳው ላይ ሳር ሰግስጎ ጥጃ አስመስሎ ይሰፋዋል፡፡ ሰው ሰራሽ ጥጃዋ ላይ አሞሌ ይቀመጥና እናቷ ጨውን እየላሰች፣ በሰው ሰራሽ ጥጅ እየተታለለች ወተቷ ይታለባል፡፡ ለእኔም ገበሬው ህወሓት፣ ሰው ሰራሽ ጥጃው ደግሞ ብአዴን ነው፡፡ በሰው ሰራሽ ጥጃ ወተቱ የሚታለበው ደግሞ የአማራ ህዝብ ነው፡፡ አሁን ላሚቱ በሰው ሰራሽ ጥጃ መታለሏን አቁማ አዲስ ጥጃ ልትወልድ፣ የታሰረችበትን ገመድ በጥሳ የራሷን ልጅ ልታጠባ የግድ ነው፡፡ ሰዓቱም ነው፡፡
በተለይ ወጣቱ ጥጃ ሆነህ እንደ እናት ያቀፈህን ህዝብ ወክለህ የምትቆምበት፣ የተጠመደብህን ቀንበር ሰብረህ የምትጥልበት ወቅት ነው፡፡ የህወሓት ስሪት የሆነው ብአዴንን ‹‹አትወክለኝም፡፡ ነቅቼብሃለሁ›› የምትልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ግፍ፣ በደልና ጭቆና ይበቃል፡፡ አሁን የአማራ ህዝብ ጉዳይ የዴሞክራሲ ሳይሆን የመኖር ያለመኖር ጉዳይም ጭምር ሆኗል፡፡
በ1997 ዓ.ም ኢህአዴግ ‹‹ኢንተርሃምዌይ›› የሚለውን ክፉ ቃል ሲጠቀም ከራርሞ፣ ሰሞኑን ደግሞ እነ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተጠቅሞበታል፡፡ አሁንም ‹‹እገሌ ሲጨቁንህ ነበር›› እያሉ ነው፡፡ እናም ብአዴንን ሆይ! በጉፈላ ላም ስመስልህ ከገዳዮች ጋር አብረህ በመሆን የገደልከው፣ ያስጨረስከው፣ ታሪክና ማንነቱን ያዋረድከውን ህዝብ ከ35 አመት በኋላ አዳኝ፣ ወኪሉ መስለህ መቅረብህ ባይዋጥልኝ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ መፅሃፍ አርዕዮስ ሁለት ምላስ ሆናችሁ ትናንት ሌላ፣ ዛሬ ሌላ ትዘባርቃላችሁ፡፡ መዘባረቃችሁ ከውስጥ አለመሆኑንም እሩቅ ሳንሄድ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ‹‹ለሃጩን እያዝረከረከ፣ በባዶ እግሩ እየሄደ ትምክት የሚተፋ›› ብሎ የተሳደበውን አቶ አለምነው መኮንን በአመራር ደረጃ ያውም የብአዴን የህዝብ ግንኙነት አድርጎ ማስቀመጡ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡ ጉዳዩ ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› ነው፡፡
በዓሉ የህወሓት ወይንስ የብአዴን
35ኛ በዓላችሁን ልታከብሩ ሸር ጉድ እያላችሁ መሆኑን እስር ቤት ሆኘም በቴሊቪዥን እየተከታተልኩ ነው፡፡ በዓሉ ከብአዴን ምስረታ ጀምሮ ተቆጥሮ መሆኑ ደግሞ ግርምትን ይጭራል፡፡ ለመሆኑ የኢህዴን/ብአዴን አላማና ተልኳቸው ለየቅል አይደለም? ኢህዴን ተቀጥቅጦ ብአዴን የተባለው መአህድ መመስረቱን ተከትሎ አልነበረም? እንደ እኔ በዓሉን ማክበር ያስፈለገው፡-
• የስልጣን እድሜን ለማራዘም
• ጭቆናው ያንገፈገፈውን ህዝብ ግፊት ለማቀዝቀዝ
• የኢትዮጵያ አንድነትን ወደኋላ ለመጎተት
• ከህወሓት ጋር ቁመት በመለካካት፣ እኩል እንደሆኑ ለማስመሰል ነው
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ ‹‹ኢህዴን/ብአዴን የማንም ውራጅ አይደለም፡፡›› ቢሉም አሁንም ግን ብአዴን የህወሓት ውራጅ ነው፡፡ በመሆኑም ብአዴን የአማራነትን ጭምብል አጥልቆ የቆመ በመሆኑ በዓሉ የህወሓት በዓል ነው፡፡ የህወሓትና የብአዴን ልደት በ11 የሚከበር በመሆኑም በአንድ ላይ ቢያከብሩትም ባልከፋ፡፡
ማን ይናገር……
የአማራ ህዝብ ይህን ያህል ገፈት ሲቀምስ ቆምኩለት የሚለው ብአዴን ዛሬ በአዲስ ስልት ‹‹ጨቋኝ አይደለህም›› ‹‹ለዴሞክራሲና አንድነት ትተጋለህ››….በሚል አዲሱን ወይን በአሮጌው አቅማዳ ይዞ፣ ከፊት ለፊት ቆሞ ሲያርድና ሲያሳርድ የነበረው ህዝብ በአዲስ ስልት ከጀርባ ቆሞ ሊያርደውና ሊያሳርደው መዘጋጀቱን የሚያሳይ ነው፡፡
ዛሬ በየሄደበት ‹‹ጡት ቆራጭና ጨቋኝ›› እየተባለ የሚሳደደውና የሚሰቃየው ህዝብ በአማራነቱ፣ በኢትዮጵያዊነቱ፣ ወኪል ቢኖረው ኖሮ ብአዴን ፅ/ቤት ላይ ተሰብስቦ ሲያለቅስ ምላሽ ባገኘ ነበር፡፡ እነ መላኩ ፈንታ ‹‹ምላሽ ይሰጣቸው›› በማለታቸው ወደ ዘብጥያ ተወርውረዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አማራ በመሆናቸው ብቻ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው (አማራ ማለት ሽብር ሆኗልና) ጥቂት የቂሊንጦ ነዋሪዎችን ስም ዝርዝር ላካፍላችሁ፡-
1. በእነ አለላቸው አታለለ የክስ መዝገብ 5 ሰዎች
2. በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
3. በእነ ዘመነ ምህረት የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
4. በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ 16 ሰዎች
5. በእነ አበበ ካሴ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
6. በእነ አስማረው አሰፋ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
7. በእነ ታደሰ ፈረደ የክስ መዝገብ 5 ሰዎች
8. በእነ ገ/ሚካኤል ገ/ስላሴ የክስ መዝገብ 9 ሰዎች
9. በእነ ነገደ ሸዋቀና የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
10. በእነ አጥናፉ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
11. በእነ አበበ ተመስገን የክስ መዝገብ 12 ሰዎች
12. በእነ መብራቴ ይርጋ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
13. በእነ ሁሴን አሊ የክስ መዝገብ 4 ሰዎች
14. በእነ አበበ የኋላ የክስ መዝገብ 4 ሰዎች
15. በእነ አዳሙ ታዬ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
16. በእነ ፀጋው አለሙ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
17. በእነ ቸሬ ተክሉ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
18. በእነ ሰጠኝ ሙሉ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
19. በእነ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
20. በእነ አንተነህ የክስ መዝገብ 2 ሰዎች
21. በእነ አቤል ከበደ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
22. በእነ አብርሃም ሞገስ የክስ መዝገብ 6 ሰዎች
23. በእነ ማስረሻ ታፈረ የክስ መዝገብ 9 ሰዎች
24. በእነ ሊጋባው ግርማ የክስ መዝገብ 3 ሰዎች
25. በእነ ፋንታሁን የክስ መዝገብ 7 ሰዎች
26. በእነ ተፈራ በላይ የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
27. በእነ አስቻለው የክስ መዝገብ 10 ሰዎች
28. ………እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ በታች የምዘረዝራቸው ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ የሚገኙ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ናቸው፡፡
1. አለማቸው ማሞ የ60 አመት አዛውንት
2. ፀጋው ካሳ የ78 አመት አዛውንት
3. ቢሆነኝ አለነ የ60 አመት አዛውንት
4. አዋጁ አቡሃይ የ75 አመት አዛውንት
5. የሻለቃ ሰጠኝ ሙሉ የ75 አመት አዛውንት
6. ወርቁ አያሌው የ67 አመት አዛውንት
7. ይርጋ አሳምረው የ68 አመት አዛውንት
8. በላይ ብሩ የ68 አመት አዛውንት ናቸው፡፡
ከላይ በስም ከጠቀስኳቸው ውስጥ ማስረሻ ሰጠኝ፣ አንተነህና አቤል ከበደ የአየር ኃይል አብራሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሌሎች ጋር የተከሰሱት የአማራ ተወላጆች፣ ከቂሊንጦ ውጭ የሚገኙት (በማዕከላዊ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ፣ አማራ ክልልና ውጡ እየተባሉ በሚባረሩባቸው አካባቢዎች) በስቃይ ላይ የሚገኙትን አይጨምርም፡፡ ይህን ፅሁፍ በማዘጋጅበት ወቅት እንኳን አማራ ወደሚሰቃይበት ማዕከላዊ እስር ቤት ከ100 በላይ የሚሆኑ አዲስ ‹‹ሽብርተኛ›› ወጣቶች ከጎንደርና ጎጃም ተለቅመው እንደገቡ መረጃ ደርሶኛል፡፡ እና የ35ኛው የብአዴን በዓል ለአማራ ህዝብ ምኑ ነው? ህዳሴ? ኩነኔ?
አበቃሁ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ይድረስ ለሀፍረተ ቢሱ ብአዴን እና ለ35ኛ በዓል አክባሪዎች (ግልፅ ደብዳቤ ከቂሊንጦ እስር ቤት)ዘመነ ምህረት (የቀድሞው መኢአድ ም/ፕሬዝደንት)
ጆሮዎች ሆይ ንቁ ! አዲስ ሙዚቃ እየመጣላችሁ ነው ። (ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)
የማውቀውን ነው የምናገረው ፤ ያመንኩበትን ነው የምመሰክረው ።
የድምፃዊት ሀሊማ አብዱራህማን 2ኛ አልበም ከቀናት በኋላ ይወጣል ። በእኔና አልበሙን ሰምተው በመሰከሩ ( እኔም ምስክርነታቸውን በማምንላቸው ሰዎች) ሙያተኞች እምነት ለጆሮ ልዩ ጣዕም የሚፈጥር ሙዚቃ ያሰማል ። አልበሙ በወጣ ጊዜ የሙዚቃ አድማጩ በየሚወጡ አልበሞች ላይ ያላገኘውን ሙሉ እርካታ ያገኛል ። ሀሊማ አብዱራህማንን በዚህ አልበም እንደ አዲስ እንተዋወቃታለን ብዬ አምናለሁ ። ፕሮዲዩሰሩ ( ከሀሊማ ጋር) ፣ ግጥምና ዜማ ደራሲው ለራሱ በገለፅኩለት ቋንቋ ብጠቀም ወደፊትም በዚህ መጠን ሙሉና ጥግብ የሚያደርግ አለበም የሚሰራ እስከማይመስል ድረስ ሰርቶታል ። በቁጥር 15 የሚሆኑ ሥራዎች የተካተቱበት ይህ አልበም ተወዳጅ ይሆናል ብዬ የምገምተው በብዙ አልበሞች ላይ አንደሚሆነው ከሙሉው አልበም 4 እና 5 ሥራዎቹ ተወደውለት አይሆንም ። ሙሉ ሥራዎቹ በሙሉው አድማጭ ይወደዳሉ ማለት የሰዎችን የፍላጎት ልዩነት ማጥፋት ይሆናል ። ሙዚቃን ለሚያጣጥሙ ( በእውቀትም በስሜትም) አብዛኛዎቹ ሥራዎች ጥዑም እንደሚሆኑ ለእኔ አያጠራጥርም ።
የዘፈን ግጥሞች ላይ ብዙውን ጊዜ ስሜቶች እንጂ ሀሳቦች ጎልተው አይወጡም ። በዓለማየሁ ደመቀ የዚህ አልበም የግጥም ሥራዎች ላይ ግን ሀሳብም ስሜትም ከፍ ባለ ደረጃ ቀርበዋል ። ከተቃራኒ ጾታ ፍቅር ወጣ ብሎ ባህልና ታሪክ ፣ ሌሎች ማህበራዊ እውነታዎች ተገልፀውበታል ። ካሁን ቀደም በሀሊማ አዘፋፈን ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በዚህ አልበም መልስ አግኝተዋል ብዬ አምናለሁ ። ድምጿንም ሆነ አልበሟን መውደድ ግን የግለሰቡ ምርጫ ነው ። ፈረሱን ወደ ወንዙ መውሰድ ብቻ ነው የሚቻለው ። አስገድዶ ማጠጣት አይቻልም ። ይህን አልበም በቅርበት እንደሚያውቀው ሰው ፣ ቢያንስ ለሁለትና ሦስት ዓመታት ያለመሰልቸት እንዳደመጠው ሰው ምስክርነቴን ( ያለማንም አስገዳጅነት ወደጄና ፈቅጄ እንዲሉ ¡ ) ሰጥቻለሁ ። ነገ አልበሙ ሲወጣ በሰጠሁት ቃል እንደማላፍር ስለማምን ነው ይህን የምለው ። ይህን ጽሑፍ ለሚያነቡ ከእኔ ባልተለመደ መልኩ ለአልበሙ ማስታወቂያ እየሰራሁ ሊመስልብኝ ይችላል ። ይምሰል ። በእርግጥም አዎን ማስታወቂያ ነው የሰራሁት ። ያስተዋወቅኩት ግን እውነቱን ነው ። እውነት ባይሆን ጥቂት እኔን የሚያምኑኝ ሰዎች ተታለው ሊገዙ ይችላሉ ። እሱ ግን የትም አያደርስም ። በማስታወቂያ ብዛት አልበሙ መውጣቱን ለሁሉም ማሳወቅ ይቻላል እንጂ አልበሙን አያሸጥም ። ይህን በተለያየ ጊዜ አይተን ፣ አረጋግጠን ታዝበናል ። ለዚህ ነው በድፍረት ቃሌን የምሰጠው ።
(ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ )በአገዛዙ የአፈና መዋቅር የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የእኩልነት ትግል አይቀለበስም!
ህወሓት/ኢህአዴግ በህገ መንግስቱና በሌሎች ራሱ ባወጣቸው ህጎች በርካታ መብቶችን ለይስሙላ ቢደነግግብ ቅሉ፤ በተግባር ግን እነዚህን መብቶች ሆነ ብሎ ባደራጀው የአፈና መዋቅሩ እየደፈቃቸው ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን አገዛዙ የመደራጀት መብትን በወረቀት ቢያሰፍርም ‹‹እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን፤ እግር ሲያወጡ ግን እንቆርጣለን›› በሚል መርህ ፓርቲዎችን በዚሁ የአፈና መዋቅሩ በገሃድ እያፈረሰ ቀጥሏል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ፈቅጃለሁ ቢልም ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በማሳደድና ሚዲያዎችን በመዝጋት አማራጭ ሀሳብ እንዳይራመድ አድርጓል፡፡ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ወረቀት ላይ ቢደነግግም በአስተዳደራዊ መዋቅሩ መሰረት ክርችም አድርጎ ዘግቶታል፡፡ የዜጎችን የመዘዋወር መብት ቢደነግግም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፓስፖርት በመንጠቅ ጉዟቸውን በማተጓጎል ላይ ይገኛል፡፡ የመንግስት አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት አለበት ተብሎ ተደንግጓል፤ ነገር ግን በየ መስርያ ቤቱ ያለ እጅ-መንሻ ዜጎች አገልግሎት ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህ ሁሉ አፈና ሆነ ተብሎ ታስቦበት፣ የአገዛዙን ስልጣን ለማራዘም የሚደረግ መዋቅራዊ ጫና መሆኑን ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡
ዛሬ በሀገራችን ከፍተኛ ርሃብ፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስራ አጥነት፤ ስደት እና ሌሎችም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶች በሰፊው ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ወቅታዊ ጉዳዮች ከህዝብ ጋር ተወያይቶ አቋም ለመውሰድና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመሰንዘር ህዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የእውቅና ደብዳቤ ለማስገባት በተደጋጋሚ ጥረት ያደረግን ቢሆንም የአፈና መዋቅሩ የእውቅና ደብዳቤውን መቀበል ባለ መፈለጉ ለ5 ጊዜ ተጉላልተን በ6ኛው በሪኮመንዴ(በፖስታ) ለመላክ ተገደናል፡፡
የእውቅና ደብዳቤው በሪኮመንዴ የደረሰው አስተዳደሩ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ላይ ሆኖ ‹‹ህዳር 18/2008 ዓ.ም አልፏል›› በሚል ለተጨማሪ ጊዜ ደብዳቤውን ሳያስተናግድ ቀርቷል፡፡ ህዳር 18 ያላለፈ መሆኑን ካስረዳን በኋላ ለሶስት ቀናት በተደጋጋሚ ብንመላለስም ‹‹ከደህንነትና ፖሊስ ጋር ካልተመካከርኩ እውቅና አልሰጥም›› ሲል እምቢታውን ገልጾአል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአባላትና ደጋፊዎቻችን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ልናደርገው የነበረው ውይይት ሊደናቀፍ ችሏል፡፡
ከዓለም የነጻነት የትግል ታሪክ እንደምንገነዘበው በአገዛዝ አፈና የተገታ የህዝብ ጥያቄ ኖሮ አያውቅም፡፡ አፈናው የነጻነትን ጊዜ ቢያዘገይ እንጅ ፈጽሞ ሊያስቀርም አይችልም፡፡ ስለሆነም ጭቆናው ወደ ነፃነት የሚያስኬደውን ጉዞ እልህ አስጨራሽ ከማድረግ በቀር ዘላቂነት ኖሯቸው የነጻነት ጥያቄውን ፈጽሞ ማዳፈን እንደማይችሉ አገዛዙ ሊረዳ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ለማይቀረው የነፃነት ትግል ቆርጦ እንዲነሳና ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ
‹‹ቆሻሻ ስድባቸው አጥንት ይሰብራል›› አበበ ኡርጌሳ
ሚያዝያ 2006 ዓ.ም ላይ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ችግር ነበር፡፡ በዚያ ወቅት እኔ ሀሮማያ ነበርኩ፡፡ ያኔ አንተ ነህ ችግር የምትፈጥረው ተብዬ ታስሬ ነበር፡፡ ግን ከቀናት በኋላ ተፈታሁ፡፡ ስፈታ ወደ ሸዋ መጣሁ፡፡ እዚህ መጥቼ ግን ሰላም አልነበረኝም፡፡ ደህንነቶች እየደወሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ስራ ለመፈለግ ከአክስቴና ከእህቶቼ ጋር ነበር የምኖረው፡፡ ግንቦት 17/2006 ዓ.ም ጠዋት አክስቴ ቤት አልነበረችም፤ እኔ ቤት ውስጥ ፊልም እያየሁ ሳለ በሩ በኋይል ተደበደበ፡፡ ተነስቼ መጋረጃውን ገለጥ አድርጌ ሳይ በፖሊስና በደህንነት ተከብቤያለሁ፡፡ ቤቱን ሳልከፍት ትንሽ ቆየሁ፤ በሩን በጉልበት ሊገነጥሉት ሲሆን ከፈትኩላቸው፡፡
በሩን ከፍቼ ወጣ እንዳልኩ አንዱ ደህንነት በቡጢ መታኝ፡፡ ወዲያው በራሴ ቀበቶ እጆቼን የፊጥኝ አሰሯቸው፡፡ እግሬንም አሰሩኝ፡፡ አካባቢውን በደንብ ቃኘት ሳደርግ ስድስት መኮኖችና 18 ፖሊሶች እንዲሁም 8 ደህንነቶችን (ሲቪል የለበሱ) ቆጠርኩ፡፡ ይሄ ሁሉ እኔን ለመያዝ ነው ብዬ ተከረምኩ፡፡ እመቤት የምትባል እህቴ ‹‹ወንድሜን አትሰሩት›› በማለቷ ደብድበዋታል፡፡ ደጅ ላይ አስረው ትንሽ ከቆዩ በኋላ (ይደዋወላሉ፣ ይጠቃቀሳሉ) ተሸክመው መሀል ላይ ካለው መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ለምን አሰሩኝ፤ ራሴ መኪና ውስጥ እገባላቸው ነበርኮ እያልኩ አስባለሁ፡፡
መኪና ውስጥ አስገብተውኝ ትንሽ እንደተጓዝን ደግሞ መኪኖችን ወዲህና ወዲያ ካሽከረከሯቸው በኋላ ዓይኔን ሸፍነው ሌላ መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ሁኔታው ሁሉ ድብልቅልቅ ሲልብኝ ይታወቀኛል፡፡ የሆነ ቦታ ስንደርስ ‹‹እኛ እንኳን አንተን…›› እያሉ መኪናው ላይ ይደበድቡኝ ጀመር፡፡ ዓይኔ ስለተሸፈነ ወዴት እየወሰዱኝ እንዳለ አላውቅም፡፡ ከዚያ የሆነ ቦታ ወስደው ሲያወርዱኝ ይታወቀኛል፡፡ እዚያ ቦታ ለአምስት ቀናት ያህል ዓይኔን እየሸፈኑ ደብድበውኛል፡፡ ደሞ ከዱላው በላይ ቆሻሻ ስድባቸው አጥንት ይሰብራል፤ ‹‹እናትህ እንዲህ ትሁን…ምናምን…›› እያሉ ይሳደባሉ፡፡
የተያዝኩ ለታ ማታውን ሲደበድቡኝ ነበር ያደሩት፡፡ በድብደባው ምክንያት ኩላሊቴን ታመምኩ፡፡ ሽንቴን መቆጣጠር አልችልም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የነበርኩበት ክፍል ጠረኑ ደስ አይልም ነበር፡፡ በጣም ስታመምባቸው ጊዜ ዓይኔን እየሸፈኑ ሀኪም ቤት ሁለቴ ወስደውኛል፡፡ ግን ስመለስ ድብደባው አይቋረጥም፡፡ ሀኪም ቤቱ የት እንደነበር አላውቅም፡፡ አንዴ ሀኪሟን ‹‹የት ነው ያለሁት›› ብየ ስጠይቃት ‹‹ያመጡህን ሰዎች ጠይቃቸው›› አለችኝ፡፡
በዚህ ሁኔታ የማላውቀው ስፍራ ለአምስት ቀናት ስቃየን ካየሁ በኋላ ግንቦት 22/2006 ዓ.ም ወደ ሌላ ስፍራ ተወሰድኩ፡፡ ለካ አሁን የተወድኩበት ቦታ ማዕከላዊ የሚባለው ኖሯል፡፡ ይሄንም ሰዎች ናቸው የነገሩኝ፡፡
ዘመዶቼ ሞቷል ብለው ነበር የሚያስቡት፡፡ ከተያዝኩ ጀምሮ እስከ ሰኔ 2/2006 ዓ.ም የት እንዳለሁ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ አንድ የሚያውቀኝ ሰው ማዕከላዊ አይቶኝ ነው ለዘመዶቼ ደውሎ ያለሁበትን ቦታ የነገረልኝ፡፡
ምንጭ ኢትዮጵያ ሂዩማን ራይትፕሮጀክት
‹‹የሚያስሩኝ ሰዎች ሲከብቡኝ እኔ ስለቶርቸርና ስለታሰሩ ሰዎች ዜና እያነበብኩ ነበር›› ባህሩ ደጉበእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት የተከሰሰ
‹‹የሚያስሩኝ ሰዎች ሲከብቡኝ እኔ ስለቶርቸርና ስለታሰሩ ሰዎች ዜና እያነበብኩ ነበር›› ባህሩ ደጉ
ዕለቱ ቅዳሜ ሀምሌ 5/2006 ዓ.ም ነበር፤ ጠዋት ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በጠዋት ከቤቴ ወጥቼ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጬ ቅዳሜ የወጡ ጋዜጣና መጽሄቶችን እያነበብሁ ነበር፡፡ በተለይ ስለ ዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ስለ ፖለቲካ አመራሮች መታሰር የተጻፈ እንዲሁም ማዕከላዊ ስለሚፈጸም ቶርች ነበር እያነበብኩ የነበረው፡፡ ለካ እኔ ይሄን የእስርና የቶርች ዜና እያነበብኩ እያለ በሚያስሩኝ ሰዎች ተከብቤያለሁ፡፡ ቀና ስል በሁለት መኪና ሆነው ፖሊሶችና ደህንነቶች አጠገቤ ቆመዋል፡፡ ዞር ስል ዙሪያየ ተከብቧል፡፡
መጀመሪያ ከበባው ለእኔ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ደንገጥ ብየ ሁኔታውን ሳስተውል ሁሉም ዓይናቸው እኔ ላይ ነው፤ ሳነበው የነበረው ታሪክ እኔም ላይ ሊሆን ነው አልኩ በውስጤ፡፡ ትንሽም ሳይታገሱኝ የከበቡኝ ሰዎች ወደ እኔ በመምጣት እጄን እና እጄን በቀኝና በግራ አንጠልጥለው መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ‹‹ምንድነው? ምን እያደረጋችሁኝ ነው?›› ስላቸው አንድ ወረቀት አውጥተው አሳዩኝ፤ የእኔን እና የዳንኤል ሺበሽን ስም አየሁት፡፡ እኔ ዳንኤል ሺበሺ የሚባል ሰው በአካል አላውቅም፡፡ ግራ ቢገባኝም ያሉኝን ከመቀበል ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡
በመኪና እየበረሩ በቀጥታ ይዘውኝ የሄዱት ወደመኖሪያ ቤቴ ነበር፡፡ ቤት ስንደርስ እኔ ከመኪና ከመውረዴ በፊት ቀደም ብለው በመውረድ አካባቢውን አጠሩት፡፡ ማንም ሰው እንዳይገባ፣ እንዳይወጣ አዘዙ፡፡ መጀመሪያ ያደረጉት ደግሞ ስልክ የሚባል ነገርን ሙሉ ለሙሉ በእነሱ እጅ ማስገባት ነበር፡፡ ቤት ውስጥ የአቦ ዝክር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ እህቶቼ ቤተክርስቲያን እንደሄዱ አልተመለሱም፤ ወንድሜ ግን ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ወንድሜ በሁኔታው ግራ ተጋብቶ የሚሆነውን ቆሞ ይመለከታል፡፡ ወደቤት ውስጥ ይዘውኝ እንደገቡ ፍተሻ ማካሄድ ጀመሩ፡፡
ፍተሻው እንደተጀመረ አካባቢ ከመቶ ሜትር ገደማ ጩኸት ይሰማል፡፡ ለካ ሁኔታውን ሰምተው እህቶቼ ነበሩ ከቤተክርስቲያን በድንጋጤ እየጮሁ የሚመጡት፡፡ በእህቶቼ ጩኸት አካባቢው በጣም ተረባበሸ፡፡ ወዲያ ፖሊሶች ዝም አስባሏቸው፡፡ የእህቶቼን ሁኔታ ሳይ በጣም ነበር የተሰማኝ፡፡ ፍተሻው ረጂም ጊዜ ወስዷል፤ ወደ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ነበር ያበቃው፡፡ ፍተሻው እንዳበቃ ወደ ማዕከላዊ ይዘውኝ ሄዱ፡፡
ማዕካላዊ እንደደረስን ምዝገባ አድርጌ ወደ አንድ ቤት ወሰዱኝ፡፡ የገባሁበት ቤት በአብዛኛው የቤኒሻንጉል ተወላጆች ይበዙበት ነበር፡፡ እዚያ ቤት ውስጥ አንድ ሰውነቱ ደልደል ያለ ጎልማሳ ብቻ ነበር በአማርኛ ቋንቋ ያነጋገረኝ፡፡ ሌሎቹ በርህራሄ ዓይን ዓይኔን ያያሉ፡፡ ‹‹ምን አድርገህ ታሰርክ?›› አለኝ ያ ሰውነቱ ደልደል ያለው ሰው፡፡ እኔም ‹‹እኔ እንጃ ምን እንዳደረግሁ አላውቅም፡፡ የሆነ ሰው ጋር ነው የእስር ወረቀት እንደወጣብኝ ያየሁት፡፡ ዳንኤል ሺበሺ ነው ስሙ፡፡ እኔ ሰውየውን በአካል አላውቀውም›› ስለው ሰውየው ‹‹ዳንኤል ማለት እኔ ነኝ›› አለኝ ፈገግ ብሎ፡፡ ‹‹ውይ ወንድሜን!›› ብየ ተጠምጥሜ አቀፍኩት፤ አምባየ መጣ፡፡ የማንተዋወቅ ሰዎችን እንዲህ ሲያጠቁን ያሳዝናል፡፡
(ማስታወሻ፡- ባህሩ ደጉ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት የተከሰሰ (9ኛ ተከሳሽ) ወጣት ሲሆን ክሱም የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀጽ 7(1) የተመለከተውን መተላለፍ የሚል ነው፤ ወጣት ባህሩ ይህን የተከሰሰበትን ወንጀል እንዲከላከልም ተበይኖበታል፡፡ ወጣት ባህሩ ደጉ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ስቃይ (ቶርቸር) እንደተፈጸመበት ለፍርድ ቤት በሰጠው የተከሳሽነት ቃል ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡)
ምንጭ ኢትዮጵያ ሂዩማን ራይትፕሮጀክት
‹‹እጄን በካቴና አስረው ሲወስዱኝ የ4 ዓመት ልጄ ምርር ብላ አለቀሰች›› ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ
ያን ቀፋፊ ዕለት አልረሳውም፤ መጋቢት 12/2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ ሆኖ ነበር፡፡ ከቤቴ ወጥቼ ወደ ስራ እየሄድኩ ሳለ ትከሻየን ይከብደኝ ነበር፤ የሆነ ሰው እንደሚከተለኝ ይሰማኝ ነበር፡፡ ስራ ቦታየ ስደርስ በቀጥታ ወደ ቢሮ መግባት አልፈለግሁም፡፡ አካባቢውን ቃኘት ሳደርግ ደህንነቶችና ፌደራል ፖሊሶች በቅርብ እርቀት እየተከታተሉኝ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ወዲያው ወደቢሮ መግባቱን ትቼ ቢሮ አካባቢ ካለች አንዲት ቤት ውስጥ ገብቼ ቡና አዘዝኩ፡፡
ቡናየን አዝዤ ስጠባበቅ ሁለት ሲቪል የለበሱ ወጣቶች መጥተው አጠገቤ ተቀመጡ፡፡
ደህንነቶች እንደሆኑ ስለገባኝ አጠገቤ ተቀምጦ የነበር አንድ ወጣትን ጠቀስ አድርጌ እንኔን የምታነሳ መስለህ ፎቶ አንሳቸው አልኩት፤ አነሳቸው፡፡ አሁንም ፎቷቸው አለ ብሎኛል፡፡ ወጣቶቹ ደህነንቶች አጠገቤ ተቀምጠው ቡናየን ጠጥቼ እስክወጣላቸው ይጠብቁኝ ጀመር፡፡ እኔ ግን ሁኔታው ስለገባኝ ባለሁበት ቁጭ እንዳልኩ ብዙ ጊዜ ወሰድኩ፡፡ እነሱም ተስፋ ቆረጡ መሰለኝ ከዚያች ቡና ቤት እንድወጣላቸው ስሜን ጠርተው ‹‹አንዴ ውጭ ፈልገንህ ነበር!›› አሉኝ በኃይለ ቃል፡፡ ሁለቱም ላይ ንዴት ይታይባቸው ነበር፡፡ እኔም ሰው ከምረብሽ ብየ ተነስቼ ወጣሁላቸው፡፡
ከቡና ቤቷ ወጣ እንዳልኩ ከደህንነቶቹ ራቅ ብለው የነበሩት ፌደራል ፖሊሶች ወደእኔ ፈጠን ብለው በመምጣት በግራ እና በቀኝ ጥብቅ አድርገው ይዘው መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ለምን እንደሚፈልጉኝ እና እኔን ለመያዝ የሚያስችላቸው የፍርድ ቤት ወረቀት ካላቸው እንዲያሳዩኝ፣ ከሌላቸው ግን ህገ-ወጥ ስራ እየሰሩ እንደሆነ ነገርኳቸው፡፡ እነሱ ግን መልሳቸው ‹‹ዝም በል!›› የሚል ኃይለ ቃል ነበር፡፡ መኪና ውስጥ እንደገባሁ ቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ነበር የወሰዱኝ፡፡
ማዕከላዊ እንደደረስኩ ከመኪና ሳልወርድ ለአንድ ሰዓት ያህል ግቢው ውስጥ አቆይተውኛል፡፡ ከዚያ የብርበራ ወረቀት ይዘው፣ የሰው ኃይልም ጨምረው ወደቤቴ ወሰዱኝ፡፡ ቤት ስደርስ ልጄ እና ባለቤቴ ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ ባለቤቴ በሁኔታው ብትደናገጥም እንዲህ አይነት ነገር ሊከሰት እንደሚችል ቀድሜ እነግራት ስለነበር ወዲያው ነው የተረጋጋችው፡፡ በዚያ ላይ ባልደረባዬ ጋዜጠኛ ካሊድ መሀመድ ቀደም ብሎ ታስሮ ስለነበር እኔንም ሊያስሩኝ እንደሚችሉ ግምቱ ነበረኝ፡፡
ቤት ሲፈተሽ በጣም ረጂም ጊዜ ነበር የወሰደው፡፡ በጣም ብዙ ወረቀት ላይ እስኪደክመኝ አስፈርመውኛል፡፡ በጣም ደክሞኝ ስለነበር ውሃ ደጋግሜ እጠጣ ነበር፡፡ ቀና እያልኩ ልጄን ሳያት ፍርሃቷን አነብበው ነበር፡፡ ልጄ ሁኔታውን በፍርሃት ስትከታተልና እናቷ በተንቀሳቀሰችበት ቦታ ሁሉ አብራ እየተንቀሳቀሰች እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ፍተሻው አልቆ ከቤት ወጣን፡፡ ልጄን እና ባለቤቴን ዞሬ አየኋቸው፡፡ ወደመኪናው እንደተጠጋን እጄን በካቴና አስረው ሲወስዱኝ የ4 ዓመት ልጄ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ አንጄቴ ቢላወስም ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡
ማዕከላዊ እንደመለሱኝ ምዝገባ እንዳከናውን ከተደረግሁ በኋላ ሳይቤሪያ ወደሚባለው ቤት አስገቡኝ፡፡ እኔ ከገባሁበት ቤት ቀደም ብለው ገብተው የነበሩ እስረኞችም ከማጽናኛ ቃላት ጋር ተቀበሉኝ፡፡ ማዕከላዊ የልጄን ለቅሶ በአዕምሮዬ እያስታወስኩ ሌሊቱን እንቅልፍ እምቢ ብሎኝ አደረ፡፡
(ማስታወሻ፡- ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ በእነ ከድር መሀመድ የክስ መዝገብ 13ኛ ተከሳሽ ሲሆን ዳርሰማ ሶሪ በጋዜጠኝነት ለ18 አመታት በተለያዩ ሚዲያዎች (ሪፖርተርን ጨምሮ) ሰርታል ፡፡፡ በተያዘበት ወቅት ደግሞ ለሬዲዮ ቢላል ይሰራ ነበር፡፡)
ምንጭ ኢትዮጵያ ሂዩማን ራይትፕሮጀክት
በመላው ኦሮሚያ የተማሪዎች ተቃውሞን ሕዝቡ ተቀላቅሎታል። የመንግስት ባለስልጣናት ተከፋፍለዋል።
በሰላማዊ መንገድ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ለመቃወም በወጡ ወጣቶች ላይ የአጋዚ ጦር በወሊሶ አራት ሰዎች በጥይት አቁስሏል።
ከተማዋ የዚህ አይነት በርካታ ህዝብ ያስተናገደ ተቃውሞ ተደርጎባት አታውቅም ሲሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በመከላከያ ሰራዊት የተከበበው የባኮ ከተማ ህዝብ ድምጹን ያለፍርሐት በመግለጽ መብቱን እየጠየቀ ነው። በተለያዩ ቦታዎች የሞቱና የቆሰሉ ተማሪዎች ቁጥር የጨመረ ሲሆን በሐረር ፤በወለጋ፣አርሲ፣ባሌ፣ጅማ፣በሸዋ በርካታ ቦታዎች መንገዶችን በመዝጋት ለመግደል የተሰማሩትን የመንግስት ወታደሮችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሕዝቡ እየተባበረ ነው።
የሕዝቡ ጥያቄ ከቀን ወደቀን በተለያዩ ቦታዎች እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ የኃይል እርምጃ ይወሰድ የሚል ትእዛዝ የሚቃወሙ ባለሰልጣናት በየቢሮው እየተፈጠሩ ነው።”የሚገደሉት ወገኖቻችን ናቸው “የሚሉ የኦህዴድ ባለስልጣናት ” ከፌደራል መንግስት የሚተላለፈውን መመርያ አናስፈጽምም የሕዝባችንን ጥያቄ በኃይል አፍነን ሰልጣናቸውን ሌላ 25 አመት ለማራዘም የወንድሞቻችን ህይወት አይገበርም ። ግድያን አንደግፍም የሚሞቱት ወንድም እህቶቻችን ናቸው ። የወጣነው ከዚህ ደሀ ገበሬ ጉያ ጥይት ከታዘዘበት ህዝብ ነው ” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።
በጨፌ ኦሮሚያ ባለስልጣናት መካከል የተፈጠረው ተቃውሞው በኃይል ይቀልበስ የሚሉና ከፌደራል የተላለፈውን ትእዛዝ ለማስፈጹም ለአዲስ ሹመት የተዘጋጁትን ከሚቃወሙት ጋር ተጋጭተው ውጥረት የተፈጠረ ሲሆን የእንቢ ባይ ባለስልጣናት ስልክና የግል እንቅስቃሴ በደህንነቶች ሰር ወድቋል።
ትላንት ምሽት ከኦሮሚያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
የተላለፈው እርምጃ እንወስዳለን መመርያ ከህዝቡ ይልቅ ሰልጣናችን ይበልጥብናል ባሉ ወገኖች ብዙዎች ሳያምኑበት የተሰጠ መግለጫ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።
‹‹ማዕከላዊ ስገባ ደጋግሜ አስመልሻለሁ›› ሸህቡዲን ነስረዲን
ዕለቱ የካቲት 14/2007 ዓ.ም ነበር፤ ጠዋት ላይ ነው፡፡ በዚያ ቀን ከእህቴ ጋር ነበርኩ፡፡ በር ተንኳኩቶ ስከፍት አንድ የማውቀው ደህንነት በሩ ፊት ቆሟል፡፡ ሌሎችም ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመዋል፡፡ ወደ ኋላዬ ዞር ስል እህቴ ሀያት ነስረዲን ሁኔታውን እየተመለከተች ነበር፡፡ በሩ ፊት ለፊት የቆመው ደህንነት ወደውስጥ እየገባ ‹‹ሰላም አሊኩም›› አለን፡፡ ለሰላምታው አጸፋውን መለስን፤ የሰውየው ንግግር ቃናውን ሳየው ሙስሊም ይመስለኛል፡፡
ደህንነቱ ወደ ውስጥ ሲገባ ሌሎች ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመው የነበሩትም ተከታትለው ገቡ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የቤቱ ባለቤት ታላቅ እህታችን ሽንት ቤት ስለነበረች ያወቀችው ነገር አልነበረም፡፡ ፖሊሶችና ደህንነቶች ተከታትለው ወደ ግቢው እየገቡ እያለ ሰላምታ ያቀረበልን ሰው እኔን ‹‹ተንበርከክ!›› አለኝ፡፡ እህቴ ሀያትን ዞር ብዬ ሳያት ‹‹እንዳትንበረከክ! ለምንድነው የምትንበረከከው?›› አለች በኃይለ ቃል፡፡ ወዲያው በሀያት ንግግር የተበሳጩት ደህንነቶች ሀያትን አመናጭቀው ከእኔ አራቋት፡፡ እኔንም በኃይል እንድበረከክ አደረጉኝ፡፡
ታላቅ እህታችን ከሽንት ቤት ስትመለስ የሚሆነውን ሁሉ አየች፡፡ ብዙም አልተደነቀችም፡፡ እህቴን አናገሯትና ወደ ቤት ውስጥ ለፍተሻ ገቡ፡፡ ትንሽ ሶፋውን ገልበጥ ገልበጥ እንዳደረጉ የእህቴ ባል ዱባይ ሀገር ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ ጋር የተነሳውን ፎቶ አዩ፡፡ (የእህቴ ባልና ሲራጅ ፈጌሳ ወንድማማቾች ናቸው፡፡) ፎቶውን እንዳዩ ‹‹ቤቱ የስርዓቱ ተቃዋሚ አይደለም›› ብለው ፍተሻውን አቋርጠው ወጡ፡፡
መጀመሪያ እኔን ብቻ የሚወስዱ የሚመስሉት ፖሊሶችና ደህንነቶች ከቤት እንደወጡ ወደ እኔና ሀያት እየተመለከቱ ‹‹እንሂድ›› ሲሉ አዘዙን፡፡ ከዚያም በፒክአፕ መኪና አስገብተው ወደሆነ ጫካ ወሰዱን፡፡ እዚያ ጫካ ውስጥ ለሁለት ሰዓት ያህል ቆመን ቆይተናል፡፡ በኋላ እንደገና በመኪና ወደ እናታችን ቤት ወሰዱን፡፡ ወደ እናታችን ቤት እየሄድን ሳለ እህቴ ሀያት እጆቼን እየደባበሰች ‹‹እነዚህ ጥፍሮችህ ሊነቀሉ ይችላሉ…አይዞህ ጠንክር›› አለችኝ፡፡ ሀያት በጣም ጠንካራ ልጅ ናት፡፡ ብዙ ነገሮች በምርመራ ወቅት ሊደርሱብኝ እንደሚችሉ ትነግረኝ ነበር፡፡
እናታችን ቤት እንደደረስን ከመኪና ወርደን ወደውስጥ እንድንዘልቅ ተደረግን፡፡ እናቴ ሁኔታውን ስታይ ደነገጠች፤ ግን ደግሞ ፍተሻው ተከናውኖ ሲያልቅ የሚበላ ነገር ቀመስን፡፡
ማዕከላዊ ደርሰን ምዝገባ ካከናወን በኋላ እኔና ሀያት ተለያየን፡፡ እኔን ወደ 8 ቁጥር ቤት ነበር የወሰዱኝ፤ ጨለማ ክፍል ነው፡፡ ልክ ክፍሉ ውስጥ ስገባ ባዶ ነው፤ አንዲት ፍራሽ ታጥፋ ተቀምጣለች፡፡ ክፍሉ በጣም ይገማል፡፡ አንድ ጥግ ላይ የሽንት እቃ አለ፤ ሽንት ሞልቶበታል፡፡ ሰገራም ሌላኛው ጥግ ላይ አየሁ፡፡ ግማቱን አልቻልኩትም፡፡ ደጋግሜ አስመለስኩ፡፡ በጣም ይቀፍ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ሽታውን ረስቼ ሌላ ሀሳብ ውስጥ ሰጠምኩ፡፡ ስለ እህቴ ሀያትም ሀሳብ ገባኝ፡፡
(ማስታወሻ፡- ሸህቡዲን ነስረዲን በእድሜ ለጋ ወጣት ሲሆን በእነ ከድር መሃመድ የክስ መዝገብ 16ኛ ተከሳሽ ነው፡፡ በዚሁ መዝገብ እህቱ ሀያት ነስረዲን 17ኛ ተከሳሽ ነች፡፡ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ ወንጀል የሽብርተኝነት ክስ ነው አቃቤ ህግ የመሰረተባቸው፡፡ )
ምንጭ ኢትዮጵያ ሂዩማን ራይትፕሮጀክት
‹‹የተያዝኩ ለታ ምግብ ሚባል ነገር አልቀመስኩም›› ጋዜጠኛ ካሊድ መሀመድ
የተያዝኩት የካቲት 11/2007 ዓ.ም በጠዋት ነበር፡፡ ገና ከጠዋቱ 12፡00 ላይ ከመስጊድ ስመለስ ሁለት ሲቪል የለበሱና ሁለት ፌደራል ፖሊሶች በመኪና ሲከተሉኝ ተመለከትኩ፡፡ ሁኔታው እንዳልገባኝ ሆኜ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡ ልክ ቤቴ ገብቼ በሩን መለስ እንዳደረግሁት የውጭው በር በኃይል ተንኳኳ፡፡ ተመልሼ ወጥቼ በሩን ስከፍት ሲከተሉኝ የነበሩት ሰዎች ተንደርድረው ገቡ፡፡ ወዲያው ወደቤቴ በመዝለቅ ስልክ የተባለን ሁሉ ሰብስበው በእጃቸው አደረጉ፡፡ ከዚያ ‹‹እንፈልግሃለን›› ብለው ይዘውኝ ሊሄዱ ሲሉ ‹‹ማናችሁ? ለምን ፈልጋችኝ ነው?›› አልኳቸው፡፡
ሰዎቹ በጥያቄየ በመገረም ‹‹አሸባሪ! ህዝብ ታሸብራለህ!›› እያሉ አጣድፈው መኪና ውስጥ ጨመሩኝ፡፡ እየሆነ ያለውን ነገር የሁለት ወር አራስ የሆነችው ባለቤቴ እንኳ መገንዘብ አልቻለችም ነበር፡፡ በዚያ በጠዋት አጣድፈው በአካባቢው ወዳለ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስገቡኝ፡፡ እዚያ ጣቢያ እያለሁ ብዙ ጥያቄዎችን ባነሳም ሰሚ አላገኘሁም፡፡ ብቻ ‹‹አሸባሪ!›› ይሉኛል ደጋግመው፡፡ እኔም ተበሳጭቼ እስከመሰዳደብ ደርሼ ነበር፡፡ 3፡00 አካባቢ ያለሁበት ፖሊስ ጣቢያ እኔን በሚያዩ ሰዎች ሲጨናነቅ ጣቢያ ቀይረው ይዘውኝ ሄዱ፡፡ ከዚያ ከቀኑ 6፡00 አካባቢ የፍርድ ቤት ወረቀት አሳይተው እንደገና ለፍተሻ ወደ ቤቴ ወሰዱኝ፡፡
ቤት እንደደረስን ቀድመው ገብተው የግቢው ሰው በሙል እንዳይንቀሳቀስ በማዘዝ ሞባይሎቻቸውን ቀሙ፡፡ ከዚያ እኔንም ይዘውኝ ወደ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ፍተሻው ተጀመረ፡፡ ያልተበረበረ ነገር የለም፡፡ እየፈተሹ እያለ ስድባቸው አይጣል ነበር፡፡ በጣም ብልግና የበዛው ስድብ ይሳደባሉ፡፡ ለአራስ ባለቤቴ እና ልጄ እያሰብኩ ለስድባቸው ምንም ላለመመለስ እሞክራለሁ፡፡
አካባቢው ሁሉ በጥበቃ ተወጥሮ ነበር፤ ማንም ወደ ውስጥም ወደ ውጭም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ፍተሻው በጣም ረጂም ጊዜ ወሰደ፡፡ ፍተሻውን ሲያጠናቅቁ እየመሸ ነበር፡፡ በግምት ወደ አንድ ሰዓት ከምሽቱ ማዕከላዊ አስገቡኝ፡፡ ማዕከላዊ እንደገባሁ ምዝገባ አከናውኜ አንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ተከተትኩ፡፡ ሙሉ ቀን ሲያጣድፈኙ ስለዋሉ በጣም ደክሞኝ ነበር፡፡ በዚያ በተያዝኩበት ዕለት ምግብ ሚባል ነገር አልቀመስኩም፡፡ ምግብ የቀመስኩት በነጋታው እኩለ ቀን አካባቢ ነበር፡፡
(ማስታወሻ፡- ካሊድ መሀመድ የራዲዮ ቢላል ጋዜጠኛ ሲሆን በእነ ከድር መሀመድ የክስ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ ነው፡፡ የተጠቀሰበት የህግ አንቀጽ የጸረ-ሽብረተኝነት አዋጁ አንቀጽ 7(1) በሽብር ወንጀል ተከስሰው ጥፋተኛ የተባሉትን እነ አህመዲን ጀበልን በኃይል ከእስር ለማስፈታት በመንቀሳቀስ›› የሚል ነው፡፡)
ምንጭ ኢትዮጵያ ሂዩማን ራይትፕሮጀክት
በሀገሪቱ በየቦታው እየተፈጸመ ያለውን ግድያ በጊዜ አቁሙ!!(በእውቀቱ ስዩም)
የሩስያ ኮሚኒስት አምባገነኖች ሕዝቡን ሰንገው በሚገዙበት ዘመን፤ አንድ ስመጥር ፈረንሳዊ ደራሲ ወደ ሞስኮ ጎራ ይላል፡፡ በጊዜው የመንግሥት ታጣቂዎች ተቃዋሚዎችን በማፈንና በመግደል ተጠምደው በማየቱ አዝኖ ቅሬታውን ላንድ ካድሬ ገለጸ፡፡ ካድሬው ቅሬታውን ከሰማ በኋላ “ እንቁላል ፍርፍር ለመሥራት ከፈለግህ እንቁላሉን መስበር አለብህ” ብሎ ተፈላሰፈ፡፡ ደራሲው የዋዛ ስላልነበረ እንዲህ ብሎ መለሰት፤ “ እዚህም እዚያም የእንቁላል ስብርባሪ ይታየኛል፡፡ ግን ፍርፍሩ የታል?”
እስከቅርብ ጊዜ ስንሰማው የነበረው፤ “ ዲሞክራሲን ቸል ያልነው ቅድሚያ ሕዝቡን ዳቦ ለመመገብ ነው” የሚለው መከራከርያ ውሃ በልቶታል ፡፡ ዳቦውም ሆነ ዲሞክራሲውም ገደል ገብቷል፡፡
የምለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ በሀገሪቱ በየቦታው እየተፈጸመ ያለውን ግድያ በጊዜ አቁሙ!! ገባሩ ህዝብ የሚላችሁን ስሙ፡፡ ስለ“ዘለቄታዊ ልማት” ለማሰብም እኮ ዘላቂ ኣገር መኖር አለበት፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት ”ሕዝብ ከሸፈተ ሠራዊት ኣያቆመውም ” ብሎ ተናግሯል፡፡ መለስ በሕይወት ዘመኑ ከተናገራቸው በጣም ጥቂት እውነቶች ኣንዱ ይህ ይመስለኛል፡፡ እናም፤ የሸፈተን ማኅበረሰብ ከመቆጣጠር ይልቅ ሰላማዊውን ሰልፈኛ በጸጥታ ማስከበር ስም በጠራራ ጸሀይ ፤ባደባባይ የሚደፉ ፖሊሶችን መቆጣጠር ይበጃል እላለሁ፡፡
ሕዝብን ሁሌ በጭራ እንደሚበረግግ ዝንብ ኣድርገው ለሚቆጥሩት ጌቶች፤ ያለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን ግጥም ጋብዤ ልሰናበት፤
“ተርብም ዝንብ ይመስላል የማይናደፍ
እስኪቆሰቁሱት፤ በሌባ ጣት ጫፍ፡፡ ”
ቅዳሜ ታህሳስ 2 ቀን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ባሉ ከተሞች በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል።
በዶር መራራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ ቅዳሜ ታህሳስ 2 ቀን ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ባሉ ከተሞች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሰልፉ እንዲገኙ ጥሪ አቀረበ።
ኦፌኮ መንግስት ራሱ በጀመረውና ባቀጣጠለው ሕገ ወጥ ሥራ የተነሳውን የህዝብ ተቃዉሞ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ ግድያን መፍትሔ አድርጎታል ብሏል።
በኦሮሞ ወጣቶችና ህዝብ ላይ የሚካሄደው ወከባ፣ ድብደባ፣ እስራትና ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ ለተገደሉትም ለቤተሰቦቻቸው ተገቢ ካሳ እንዲከፈል ወንጀሉን የሰሩትም ለፍርድ እንዲቀርቡ በቅርብ ባወጣው መግለጫ የጠየቀው ኦፌኮ ከጎንደር ገበሬዎች ተወስዶ ለሱዳን ሊሰጥ የተሳበውን ሕግ ወጥ እርምጃ ማውገዙ ይታወሳል።
“ከአማራ እና በኔሻንጉልል ጉሙዝ ክልሎች ህዝቦች እውቅና ውጭ መሬቶቻቸዉን ቆርሶ ለጎሮቤት አገር ለመስጠት እየተደረገ ያለዉን ዝግጅት አጥብቀን እናወግዛለን። በአስቸኳይ እንዲቆምም እንጠይቃለን” በማለት የጠየቀው ድርጅቱ ጥያቄውን በመግለጫ ብቻ ሳይሆን መንግት ለሕዝብ በደል ምላሹ ጥይት በመሆኑ ድርጊቱን ለማውገዝ በነገው እለት ኢትዮጵያውያን በሰልፉ እንዲካፈሉ ጥሪውን አቅርቧል።
በአንዋር መስጊድ የደረሰው ፍንዳታ በሙስሊሙ ላይ የተቃጣ እኩይ ድርጊት ነው! የሴራው አቀናባሪዎች ስሌትም አይሰራም!(ድምጻችን ይሰማ)
አርብ ታህሳስ 1/2008
በዛሬው እለት በአንዋር መስጊድ ከጁምዓ ሰላት በኋላ ቦንብ መፈንዳቱ ታውቋል፡፡ በፍንዳታው የተጎዱ ሙስሊሞችም አሉ፡፡ ለፍንዳታው ተጠያቂ አካል ማን አንደሆነ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ይህ ፍንዳታ በ1987 መንግስት በአንዋር መስጊድ ግጭት አስነስቶ በርካታ የሙስሊም መሪዎችን፣ ኡለማዎችንና ወጣቶችን ያሰረበትን ክስተት ያስታውሰናል፡፡ በአራት አመት የትግል ሂደታችን መንግስት ሰላማዊ ትግላችንን ፈር አስለቅቆ በሀይል ለመጨፍለቅ ያደረጋቸውን ሙከራዎችን እንደህዝብ ተከላክለናል፣ አክሽፈናልም፡፡
የመንግስት የደህንነት አካላት ከአወሊያ ጀምረው በየመስጊዳችን መሰግሰግ ጀምረው ነበር፡፡ ይህንን የሚያውቁት ኮሚቴዎቻችን በግልፅ ‹‹በመካከላችን የምትገኙ የደህንነት አባላት›› እያሉ መልእክቶቻቸውን ያደርሱ ነበር፡፡ ከአወልያ ጀምሮ የደህንነቱ ክፍል ኮፍያ፣ ጥምጣምና አባያ ገዝቶ በርካታ ተቀጣሪዎቹን በመስጊድ እንዲውሉ ካደረገ ውሎ አድሯል፡፡ ትንኮሳዎቹም ዛሬ የተጀመሩ አይደሉም፡፡ ብልሆቹ ኮሚቴዎቻችን በሰጡት አመራር አንድ ቅጠል ሳይበጠስ የማበጣበጥ ሴራዎች ከሽፈዋል፡፡ ተቃውሞው ወደ አንዋር መስጊድ ከተሸጋገረበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹ከዛሬ ነገ ብጥብጥ በተነሳ!›› በሚል እኩይ አላማና ጉጉት በአንዋርና ኑር መስጊዶች ዙሪያ ባሉ ህንፃዎች ላይ ካሜራ ጠምደው “የብጥብጥ ማስረጃ” ለመቅረፅ ለብዙ ጊዜ ቋምጠዋል፡፡ ከተቃውሞ ፊት ለፊትም የአንበሳ አውቶቡሶችን እንዲሰበሩላቸውና እንዲቀረፁ ፊት ለፊት ለመደርደርም ሞክረው ነበር፡፡ ነገር ግን ህዝበ ሙስሊሙ መንግስት የሚያስብበትን አእምሮ በሚገባ አውቋልና የ1987 ክስተት በፍፁም እንዳይደገም በጥንቃቄ ተጉዟል፡፡ ይህ ቢሆንም የራሱ ደህንነቶች በሰሩት ‹‹መኪና የማቃጠል››፣ ‹‹ባንዲራ የማቃጠል›› እና ‹‹በቪዲዮ የመቅረፅ›› ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በእነዚህ በሙስሊሙ መካከል በተሰገሰጉ ደህንነቶችና ካድሬዎች ከተሰሩት ደባዎች ግን በሀምሌ 11ዱ ‹‹የጥቁር ሽብር›› ጥቃት ወቅት ያስነሱት ትንኮሳና የተሰነዘረው ጥቃት ግን ወደር አልነበረውም፡፡ በተለያዩ ክልሎችም የወንድሞቻችንን ህይወት የቀጠፉና አካልን የጎዱ ጥቃቶችን ከጁሙአ ሰላቶች መልስ ፈጽመዋል፡፡
‹‹መንግስት በዚህ ትግላችን ከተጀመረ አራተኛ ዓመት በሆነበትና ሀገሪቱ በድርቅና በተቃውሞ እየተናጠች ባለችበት ወቅት የሙስሊሙን ትግል ጥላሸት በመቀባት ትኩረትና አጀንዳን ለማስቀየር አይሞክርም›› የሚል የዋህነት የለንም፡፡ ይህንን የምንለው መንግስት እኩይ ተግባር ለማድረግ ምክንያት (Motive)፣ የመፈፀም ብቃት (Access)፣ አጋጣሚ (Opportunity) እና ያለፈ ሪኮርድ (Past Record) ስላለው ነው፡፡ ከዚህ በፊት በይፋ ያልተዋወቁና ቅፅበታዊ የተቃውሞ መርሀግብር እንኳ ሲኖር በተሰገሰጉት ደህንነቶቹ ‹‹ወረቀት ይዘህ ነበር›› በማለት ሲያስሩ እንደነበር የምናውቀው ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በተለይም በአንዋርና በኑር መስጊድ ለየት ባለ መልኩ የፖሊሶች ቁጥር ጨምሮ እንደነበርም መረጃዎች አሉ፡፡
አንድ ነገር ግልጽ ነው፡፡ ስሌቶችን በማስላትና ሴራን በማጠንጠን በቀላሉ ሕዝብን ማታለል አይቻልም፡፡ ከቅርብ ታሪካችን ተነስተን ‹‹ዋናው ተጠርጣሪያችን መንግስት ነው›› ብንልም ሌላ አካላት ሊያደርጉት አይችሉም የሚል እምነትም የለንም፡፡ ሁሉንም ግን አላህ ያውቃል! ዛሬ የደረሰውን ጥቃት ከማውገዝ ባለፈ ግን ሀይማኖታችንንና መስጊዶቻችንን የመጠበቅ ሃላፊነት ከማንም በፊት የራሳችን ሙስሊሞች ሃላፊነት ነው፡፡ አሁንም ህዝበ ሙስሊሙ በየመስጊዶቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ መስጊዶቻችንን እና አጠቃላይ ተቋሞቻችንን እኩይ ዓላማዎችን አንግበው ከሚመጡ አካላት የመከላከሉ ስራ የሰላማዊ ትግላችን አንዱ አካል ነው፡፡ የሙስሊሞች ሰላማዊ ሂደት የሚያጠለሹ ስራዎችን በአይነቁራኛ የመጠበቅ ሀላፊነትም አለብን፡፡ በየመስጊዶቻችንና በየተቋሞቻችን የተሰገሰጉ የመንግስት ደህንነትና ካድሬዎችን የማጋለጥ ሀላፊነትም በሁላችንም ላይ እንዳለብን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ አላህ በጥቃቱ የተጎዱትን ጤናቸውን ይመልስላቸው ዘንድ እንመኛለን!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር
ማስጠንቀቂያውን እንስማ፤ ኢትዮጵያ በአደጋ ላይ ናት! የሸፈተን ሕዝብ ምንም አይገድበውም!!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መግለጫ
ታኅሣሥ 1፤2008ዓም
አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ስለ ልጇ እንዲህ አለች፡ “ልጄን በጥቅምት ወር ለትምህርት ላኩት በኅዳር ሬሣውን ለቀብር ተቀበልኩ!” ይህች እናት የሁላችንንም ወላጅ እናት የምትወክል ናት፤ ኢትዮጵያን እና በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ላይ ያለውን ሁኔታም በግልጽ የምታሳይም ናት፡፡ ሟች ልጇ የሷ ልጅ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ወላጆች ልጅ፤ ወንድም የሚወክል ነው፡፡ ይህ ልጅ የእናንተን በህወሃት ውስጥ ያላችሁትን የሥርዓቱ መሪዎች፣ ተላላኪዎችና አጎብዳጆችን ልጅ የሚወክልም ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ግፍ እና ሰቆቃ በአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ላይ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ እናት ላይ እየደረሰ ነው፡፡ እናንተም እንደ ሰው ከእናት በመፈጠራችሁ ይህ ስቃይና መከራ አይደርስብንም፤ አይነካንም ማለት አትችሉም፡፡ ከሕዝብ ለመሰወር ብትሞክሩ እንኳን ሁሉን ከሚችል ፈጣሪ በጭራሽ መሰወር አትችሉም፡፡ ስለዚህ ይህ ሰቆቃ እና ስቃይ በአስቸኳይ መቆም አለበት!!
ሰሞኑን በአገራችን እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በገሃድ እየተመለከትን ነው፡፡ በተለይ ከሁለት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተወሰደው አቋም እጅግ የሚያስደንቅና የሁላችንንም ዕይታ የሳበ ነው፡፡ ተማሪዎቹ እንደተለመደው ወደ መመገቢያ ቦታቸው ሲደርሱ ምግባቸውን ወስደው በሥፍራቸው ተቀመጡ፡፡ ወደ ፈጣሪያቸው እየሞቱ፣ እየተሰቃዩና እየተራቡ ለሚገኙት ወገኖቻቸው ጸሎት አደረሱ፡፡ ከምግቡ አንዲት ቁራሽ ሳይቀምሱ ከተቀመጡበት በመነሳት ምግቡ ጠረጴዛው ላይ በመተው የመመገቢያ አዳራሹን ለቅቀው ወጡ፡፡ 15 ሚሊዮን ወገናቸው እየተራበ፣ ሌላው ደግሞ እየተፈናቀለ፣ እየተገደለ፣ የመኖር ኅልውናውን እያጣ በሰላም እየበሉ ለመኖር እንደማይፈቅዱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ አሳዩ፡፡
ተማሪዎቹ ስለወሰዱት እርምጃ ብዙ መባል ቢችልም ይህ ዓይነቱ የሰላማዊ ተቃውሞ ደም በማፍሰስ ከፍተኛ ብቃት ላካበተው የህወሃት ጠብመንጃ አንጋች የሚመቸው አካሄድ አይደለም፡፡ ሰላማዊ ትግል ማለትም ምን ማለት እንደሆነ ተማሪዎቹ በገሃድ አሳዩ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በሌሎች ከፍተኛ ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችም ተመሳሳይ ዕርምጃዎች በመውሰድ ለወገናቸው ያላቸውን ተቆርቋሪነት በግልጽ አሳይተዋል፡፡ የዝቅተኛ ትምህርት ተማሪዎች፣ የሆስፒታል ሠራተኞች፣ የተለያዩ መ/ቤት ሠራተኞችና ነዋሪዎችም ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ በማድረግ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ መሆኑን በሌላ ደግሞ የሰላማዊ ትግል ብቃትና ፍሬያማነት አሁንም በኢትዮጵያ መሥራት እንደሚችል እያስመሰከሩ ነው፡፡
ኢትዮጵያን እንደ እህል በዘር መደብ ከፋፍሎ እየገዛ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) የትግራይ ሕዝብን በፍጹም የማይወክል ቢሆንም አሁንም “በነጻ አውጪ” ስም አንድን ክልል ለማስገንጠል በቆመ ዓላማ ኢትዮጵያን በግፍ እየገዛ ነው፡፡ ከአነሳሱ ጀምሮ በራሱ ውስጥ የነበሩና አሠራሩንና ዓላማውን የተቃወሙትን ሁሉ በመግደል፣ በማሰር፣ በማሰቃየት የጀመረው በሟቹ መለስ ዜናዊ የተመራው ህወሃት ጨካኝነቱን ነጻ አወጣዋለሁ ባለው ሕዝብ ላይ አለገደብ ሲያሳይ ከቆየ በኋላ ወደ ሥልጣን መንበር ሲመጣ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ዘመቻውን አድርጓል፡፡ ሲጀምር አማራ ብሎ የሰየመውን ሕዝብ ማጥቃት ተያያዘ፤ ቀጥሎም ከአርባ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያ በውድ ያስተማረቻቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የከፈሉትን ዋጋ እንኳን ከቁም ነገር ሳይቆጥር በሁለት መስመር ደብዳቤ ከማስተማር ሙያቸው አባረረ፡፡ ግፉ ቀጠሎ ሲዳማዎችን፣ አኙዋኮችን፣ ለቅንጅት ድጋፍ የወጡ ሰልፈኞችን፣ በዖጋዴን ሶማሊዎችን፣ አፋሮችን፣ ማጃንጂሮችን፣ ቤንሻንጉልና ጉምዞችን፣ የኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎችን፣ በደቡብ በርታዎችን፣ በሱዳን ጠረፍ የሚገኙ ገበሬዎችን፣ ሙስሊሞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የዴሞክራሲ አራማጆችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የተቀናቃኝ ፓርቲ አመራሮችን፣ የከተማ ነዋሪዎችን፣ ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ ቆይቶ አሁን ደግሞ ከዚህ በፊት ያደረሰው መከራ ሳያንሰው በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የበቀል በትሩን እየዘረጋ ነው፡፡
ይህ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ብቻ የተቃጣ ሳይሆን ሁላችንም በእያንዳንዳችን ላይ እንደተቃጣ ግፍ አድርገን ልንወስደው ይገባናል፡፡ የሚፈሰው የኦሮሞ ደም አይደለም፤ የሰብዓዊ ፍጡር እንጂ፡፡ ዘር፣ ጎሣ፣ ወገን፣ … የተለያየ ደም የለውም – ሁሉም ሰው በፈጣሪ በእኩልነት የተፈጠረ የአምላክ ድንቅ ሥራ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ትግሉም፣ ተቃውሞውም የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሰዎችንም ጨምሮ የመላው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አለበለዚያ የወገንና የጎሣ አድርገን የምንወስደው ከሆነ ከዚህ በፊት እንደተካሄዱት በአንድ ወቅት ተነስቶ የሚጠፋ ወደሌላው ቦታ ለመቀጣጠል የማይችል፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ውክልና የሌለው፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ የሚበልጥ፤ ጭፍን፣ ጠባብና ለህወሃት ዕድሜ ማራዘሚያነት የሚያገለግል ቶሎ የሚዳፈን ግብታዊና ወቅታዊ ዓመጽ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ስለዚህ ይህንን የሕዝብ እንቅስቃሴ በሰብዓዊነት መነጽር ለማየት የማይፈልጉ ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል፡፡ ጎሣቸውን ወይም ሕዝባቸውን ነጻ እናወጣለን ብለው ህወሃት ካደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ውድመት ሊያደርሱ እንደሚችሉ በጥብቅ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን “እኔን አይመለከተኝም” በሚል አስተሳሰብ ከዳር ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ ትግሉን ጎሣዊ ለማድረግ ከሚመኙት ያልተናነሰ ጉዳት እንደሚያደርሱ እነርሱም በጥንቃቄ ሊያዩት ይገባል፡፡ የአንድ ሰብዓዊ ፍጡር ደም መፍሰስ የራሳቸው እንደሆነ አድርገው ካልወሰዱት ጉዳቱ የራሳቸውን በር ሲንኳኳ የሚደርስላቸው ያጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዳትኖር ወደማድረግ የሚያደርስ የጥፋት ቁልቁለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) “ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነትን እናስቀድም” በሚል መሪ መፈክር አንቅስቃሴውን የሚያካሂደው፡፡ ከሰብዓዊነት በፊት ጎሣን፣ ወገንን፣ ዘርን፣ … ማስቀደም ህወሃትን መልሶ በሥልጣን ማስቀመጥ ነው፡፡
በሕይወት በነበሩ ጊዜ ኢትዮጵያን በጎሣ ከፋፍለው ሲያበቁ በሕዝብ ለመወደድ ብለው “ሕዝብ ከሸፈተ ሠራዊት አያቆመውም” የሚል ንግግር መለስ ዜናዊ ስለማድረጋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ ሕዝብ ያሉት ለተገንጣይ ቡድናቸው ድጋፍ ይሰጣል ያሉትን ሊሆን ቢችልም አነጋገራቸው ግን አሁን በአገራችን ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ እውነትነት አለው፡፡ ህወሃት ሁሉንም ሲያደማ ስለኖረ አሁን ሕዝብ ሸፍቶበታል፡፡ ይህንን ሐቅ ማመን ስላልፈለገ ግን ሠራዊት አሰማርቶ የሕዝብን ቁጣ ለማፈን የሚቻለውን ሙከራ እያደረገ ነው፡፡ ሌጋሲያቸውን እንጠብቃለን እያለ በሙት መንፈስ የሚመራው ህወሃት መሪው ያሉትን ቃል ቢሰማ ጥሩ ነው፡፡ እስካሁን ያሠማራውም ሆነ ወደፊት ሊያሰማራ ያሰበውን ሠራዊት ሁሉ ቢጠቀም ሕዝብ እስከሸፈተበት ድረስ በየትኛውም ዓይነት ሠራዊት ሊያስቆመው አይችልም፡፡
ህወሃት “ትጥቅ ትግል” ባለው የበረሃ ጉዞው ላይ በጠብመንጃ አፈሙዝ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሲያገኝ እንደነበረው ሳይሆን አሁን አገር እየገዛ ነው፤ ህንጻም፣ መንገድም፣ … ሠርቷል፤ የጦር ሠራዊት ጡንቻውንም አዳብሯል፤ ገንዘቡን ተቆጣጥሯል፤ ብዙ ዘመናትም ለመግዛት ቋምጧል፤ ሕዝብ ከሸፈተበት በኋላ ግን ዲስኩር የነፋባቸው ህንጻዎችና መንገዶች ማንንም አይሸሽጉም፤ ሠራዊት ብሎ ለራሱ ያደለበውም ኃይል ማንንም መከላከል አይችልም፤ የሸፈተን ሕዝብ ምንም አይገድበውም፤ ማዕበል ነው፤ ጎርፍ ነው፤ ሱናሚ ነው፡፡ ስለዚህ እናንት የህወሃት ሹሞች በእጅጉ ተጠንቀቁ! በንጹሃን ተማሪዎች ላይ የጠብመንጃ ቃታ እንዲሳብባቸው የምታዙትን ሠራዊት አቁም በሉት፣ ካልተባለ ነገ ቃታውን ወደ እናንተ ለማዞሩ ምንም ዋስትና የላችሁም፤ በችጋር የሚያልቀውን የኢትዮጵያ ሕዝብና ህጻናት እንደ ራሳችሁ ሕዝብና ልጅ ተመልከቱት፤ የሙት ሌጋሲ ለመጠበቅና ለልማት በሚል ከንቱ “ውዳሴና ህዳሴ” የምታፈናቅሉት ምስኪን ገበሬ ስቃይ ይሰማችሁ፣ የፈጣሪ በትር የተመዘዘ ዕለት የእናንተም ጽዋ ከዚህ እንደማያልፍ በቀረው ጥቂት የማሰብ ኅሊናችሁ ለማስተዋል ሞክሩ፡፡
አገራችን በአደገኛ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ማስጠንቀቂያው ለሁሉም ነው፡፡ በአንድ በኩል ደም ከማፍሰስና ከመግደል በቀል የአእምሮው ክፍል ምንም ማሰብ የማይችል ጨካኝ ሠራዊት በመግደል ፈንጠዝያ ላይ ነው፤ ከጌቶቹ በተሰጠው ትዕዛዝ ብዙ ለመግደልና ደም ለማፍሰስ ጠብመንጃውን ወልውሏል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አገራችንን በጎሣ፣ በዘር፣ በወገን፣ በሃይማኖት ለመከፋፈል ያሰፈሰፉ የውስጥና የውጭ ኃይላት ሕዝባዊ ዓመጹን የራሣቸው ለማድረግ ቋምጠዋል፡፡ ሕወሃት ለ24 ዓመታት ያመቻቸላቸው ዘረኝነትና ጥላቻ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው መንገዱን ወለል አድርጎ ከፍቶላቸዋል፡፡ ሁሉም ማቆም አለባቸው!!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ” በሚለው ቀዳሚ ዓላማው መሠረት “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን በስተቀር ማንም ብቻውን ነጻ መውጣት አይችልም” የሚለው መርህ አሁንም በተግባር ላይ መዋል አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም የሕዝብ እንቅስቃሴ ለራሳችሁ የግል፣ የጎሣ፣ የወገንና የሥልጣን ጥማት ማርኪያ ለማዋል ያሰባችሁ ከህወሃት ተማሩና ትግሉን ለመቀልበስ የምታደርጉትን ሙከራ አቁሙ፤ ይህ የሕዝብ ትዕይንት ነው፤ እናንተ በዘር በሽታ የተለከፋችሁ እና መፍትሔ በጠብመንጃ አፈሙዝ እናገኛለን ብላችሁ የምታምኑ የህወሃት ሰዎች ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ፤ ቀን ሳለ አሁን ልባችሁን ክፈቱና ዋይ በሉ፤ የሕዝብ ቁጣ ገንፍሎ የአምላክ በትር በእናንተ ላይ ሳይወርድ በማጭበርበርና በማታለል ወይም በውሸት ሽምግልናና ዕርቅ ሳይሆን ከልብ በመነጨ ቅንነት የሕዝብን ጥያቄ መልሱ፡፡ የገነባችሁት ሁሉ አልሰራ ብሎ በራሱ መፍረስ ከጀመረ ቆይቷል፤ ይህ ደግሞ በጥገና እና ቀዳዳ በመድፈን አይስተካከልም፡፡ የድርብ አኻዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እያላችሁ ለዘመናት ስትዋሹ የኖራችሁበት ዲሰኩር በችጋር ዓይኑን አፍጥጦ በገሃድ ታይቷል፡፡ ሁሉም ነገር አብቅቶለታል፡፡ አሁን ካለበት የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አቁሙ! የኢትዮጵያውያን ደም የፈጣሪ ደጅ ከደረሰ ቆይቷል፡፡ የእርሱን ዝምታ እንደ ስንፍና ከቆጠራችሁት የበቀል በትሩን ሲዘረጋ የገተራችሁት ፎቅና ያደለባችሁት ጦር በጭራሽ አይመክተውም፡፡ የአምላክ ፍርድ በሕዝብ ምሬትና ቁጣ ይገለጻል፡፡ ያንን ለማብረድ ጊዜው አሁን ነው፤ የጋራ ንቅናቄው በዚህ ጉዳይ ላይ ከማንኛውም ይመለከተኛል ከሚል ጋር ለመሥራት አሁንም ፍላጎቱን ያለው መሆኑን ያስታውቃል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ያላችሁ ባላችሁበት ኅብረተሰብ ዘንድ ተደማጭነት ያላችሁ ሁሉ በሁሉም መስክ ባገራችን ላይ የተነጣጠረውን መቅሰፍት ለማርገብ የሕዝብ ድምጽ መሆን የምትችሉበት ወሳኝ ጊዜ አሁን ነውና ድምጻችሁን አሰሙ፤ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከጎናችሁ ነው፡፡
አምላክ የፈሰሰውን ደማችንን ያብስልን፤ ቁስላችንን ይፈውስልን፤ ለለውጥ በግል ወይም በጥቂት ቡድን ወይም በጎሣ ወይም በዘር ሳይሆን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ለመነሳት እንድንችል ራዕይ ይስጠን፡፡ ዓይናችን እውነትን ለማየት ብርሃን ይስጠን፤ ጆሮዎቻችንም እውነትን ለመስማት የተከፈቱ ይሁኑልን፤ ኅሊናችንም እውነትን ለመረዳትና በተግባር ለማዋል የወሰነ ያድርግልን፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
__________________________________________
የበለጠ መረጃ ለማግኘት የጋራ ንቅናቄውን ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶን በዚህ አድራሻ ማግኘት ይቻላል፤ Obang@solidaritymovement.org
የአርበኞች ግንቦት 7 የመጀመሪያ ምክርቤት ስብሰባ መግለጫ
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከህዳር 26 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ህዳር 30 ቀን 2008 ዓም ድረስ ሰራዊቱ በሚገኝበት የትግል ቦታ የመጀመሪያውን የምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ በስኬት አጠናቋል::
ይህ ስብሰባ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርና ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ተዋህደው አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከተሰኘ ወዲህ የተደረገ የመጀመሪያው የምክር ቤት ስብሰባ ነው::
ይህ ስብሰባ፦
1. ውህደት ከተደረገበት ከጥር 2 2007 ዓ.ም ወዲህ የስራ አስፈፃሚውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል፤
2. ከውህደት ወዲህ ንቅናቄው የፈጸማቸውን ተግባራት በጥልቀት መርምሯል፤
3. የንቅናቄውን ህገ-ደንብና አሰራሮችን መርምሮ ማሻሻያዎችን አድርጓል፤
4. የምክር ቤቱ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል
5. ተተኪና ወጣት የአመራር አባላት ምክር ቤቱ ውስጥ እንዲካተቱ አደርጓል፤
6. የሃገራችንን የወቅቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች በጥልቀት መርምሯል፤
7. በወቅቱ ሁኔታዎች ጥናት ላይ ተመርኩዞ የወደፊት የትግል አቅጣጫውን ቀይሷል፣ ግልጽ የሆነ የትግል ስትራቴጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፤
8. ከስብሰባው በኋላ መከናወን የሚገባቸውን ተግባራት ቅደም ተከተል አውጥቶ ለስራ አስፈጻሚው መመሪያዎችን አስተላልፏል፡፡
የአርበኞች ግንቦት 7 ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሓትን አምባገነን አገዛዝ አስወግዶ በምትኩ ፍትህ የነገሰባት፣ የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት የሚያደርገውን ትግል በግንባር ቀደምትነት ለማስተባበርና ለመምራት ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት መነሳቱን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይገልጻል::
አርበኞች ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ወደ አዲስ ደረጃ ተሸጋግሯል ብሎ ያምናል:: ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችና ድርጅቶች በሙሉ በሚያመቻቸው መንገዶች እየተደራጁ ከንቅናቄያችን ጋር ግንኙነት በመፍጠር በጋራ ትግል አምባገነኑን ወያኔ ከስልጣን እንድናስወግድና በምትኩ ፍትህ፣እኩልነትና የሃገርን አንድነት የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ስርዓት እንድናቋቁም ጥሪ ያደርጋል::
ድል ለ ኢትዮጵያ ህዝብ!
ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥት የማስተር ፕላኑን ጉዳይ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈታ አሳሰቡ
በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም የተነሱትን ጥያቄዎች፣ መንግሥት በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳሰቡ፡፡
ለዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ቅድሚያ እንዲሰጥ ያሳሰቡት ፓርቲዎች የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በተናጠል ባወጡት መግለጫ ሲሆን፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ)፣ የመላ ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦዴፓ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ደግሞ በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን ከተሞችን ለማቀናጀት የተዘጋጀው የጋራ የማስተር ፕላን ላይ የተፈጠረውን ተቃውሞ አስመልክቶ መግለጫ ማውጣቱን ያስታወሰው ኢዴፓ፣ ‹‹ጉዳዩ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ እየተባባሰና አብዛኛውን የኦሮሚያ ክልል ኅብረተሰብ ባካተተ ሁኔታ መጠነ ሰፊ ተቃውሞ እየታየ ይገኛል፤›› ብሏል፡፡
‹‹በኅብረተሰቡና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በኦሮሚያ ከተሞች እየታየ ያለው ግጭት የማስተር ፕላኑ ብቻ ሳይሆን፣ በክልሉ ያለው የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ጭምር ነው፤›› በማለት፣ ‹‹የመብት ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይፈቱ›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ኢዴፓ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹መንግሥት ሕግንና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች የሚሰጣቸው መልሶች ሕግን የተከተሉ፣ የሰዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበሩ፣ እንደዚሁም በዜጎች ሕይወትም ሆነ አካል ላይ ጉዳት የማያደርሱ መሆን ይገባቸዋል፤›› ሲል ኢዴፓ አሳስቧል፡፡
ከዚህ በፊት በማስተር ፕላኑ ጉዳይ ላይ ኢዴፓ ባወጣው መግለጫ የተፈጠረውን ችግርና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲቋቋም መጠየቁን አስታውሶ፣ ‹‹ሆኖም መንግሥት ጥሪያችንን በቸልተኝነት በማለፍ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አሁንም ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከመሠረቱ የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲያጣራና የደረሰበትን ውጤት ለሕዝቡና ለፓርቲያችን ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤›› በማለት ጥያቄውን ለመንግሥት አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ ኢራፓ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ጥበብንና ዕውቀትን ለመገብየት ሲሉ በተለያዩ ደረጃዎች የትምህርት ገበታዎች ላይ የተሰማሩ ሴትና ወንድ የኦሮሚያ ቡቃያዎችንና ሌሎችንም መሰል እንቡጦች፣ ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠላቸውን መብት ተጠቅመው በሰላማዊ መንገድ ቅሬታዎችን ባሰሙት፣ እንዲሁም በወላጆችና በኅብረተሰቡ ላይ መንግሥት እስካሁን የወሰደውና በመውሰድ ላይ የሚገኘውና ነገም ሊወስድ ያለው ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ ሕገ መንግሥታዊ ስለማያስብል የሚነቀፍ ድርጊት ነው፤›› በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅትም ሆነ ባለፈው ዓመት በማስተር ፕላኑ ሰበብ የታሰሩ የኦሮሚያና ሌሎች ወጣቶችና ንፁኃን ዜጎች በሙሉ እንዲፈቱ፣ በእነዚህ ወቅቶች ውድና ብርቅ ሕይወታቸውን ያጡት የስም ዝርዝራቸው እንዲታወቅ፣ አግባብ ያለው ካሳም እንዲታሰብላቸውና የኃይል ዕርምጃ የወሰዱትም ለሕግ ይቅረቡ፤›› በማለት ኢራፓ ጠይቋል፡፡
‹‹መንግሥት ለኢንዱስትሪያላይዜሽን በመውተርተር ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወሳኝ ወቅት፣ የአገራችንን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችንና አፍራሽ ክስተቶችን በወታደራዊ ዕርምጃ ለመፍታት መሞከር ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ ከሚለው አልፎ፣ የአገሪቷን ዕጣ ፈንታ ወዳልተፈለገ ጠርዝ እንዳይገፋና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አካባቢያዊ ጣልቃ ገብነቶች የጋራ ቤታችንን በርግደው እንዲገቡ በር ከፋች ከመሆን፣ መንግሥት እንዲጠነቀቅ፤›› በማለት ኢራፓ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
‹‹ኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ለገዢው ፓርቲና ለመንግሥት ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ግልጽነት ስለሚጎድለው ጥቅሞቹንና ጉዳቱን እንዲሁም ጭራሽ መቅረቱንና ወደፊት የሚተገበር መሆኑን፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ግልጽ እንዲያደርጉና በዚህ የተነሳ አንድም የኦሮሞ ዜጋ ሕይወት እንዳያልፍ አንስተን ተወያይተንበታል፤›› ያሉት አራቱ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ አራቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በውይይቱ የተገኙ የኦህዴድ አባላትም ‘ማስተር ፕላኑ የኦሮሚያን ሕዝብ የሚጎዳ ከሆነና ሕዝባችን የማይፈልገው ከሆነ በኃይል በሕዝቡ ላይ የሚጫን ሊሆን እንደማይገባ ይፋ አድርገው ወደፊትም ሕዝቡን እናወያያለን’ የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
‹‹ይህንን ተቃውሞ ያባባሰው ጨፌ ኦሮሚያ በመጀመርያ መደበኛ ስብሰባው ያወጣውና ሕዝቡ ያልመከረበት የኦሮሚያ ማስተር ፕላን አዋጅ በመሆኑ፣ በአሁን ጊዜ መላው የኦሮሞ ተማሪዎችና መላው የኦሮሞ ሕዝብን ቁጣ የቀሰቀሰ በመሆኑ አዋጁ በአስቸኳይ እንዲሻር፤›› በማለት በጋራ መግለጫቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
‹‹ከሁለት ዓመት በላይ የኦሮሞ ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፈው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን፣ መላው የኦሮሚያ ሕዝብ ተቃውሞውን ያሰማበት በመሆኑ ዕቅዱ ቆሞ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለሕዝቡ ይገለጽ፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት ጥቃት በመሰንዘር ከፍተኛ ድልን ተቀዳጀ!!
የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት ተደጋጋሚ የሽምቅ ውጊያዎችን በማድረግ የህወሓትን መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጦር አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የህዝብ አለኝታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
ባለፈው ሳምንት ህዳር 21/2008 ዓ.ም ጀግናው ሰራዊታችን በዋልድባ በጠላት ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዋልድባ ወደ አዲ-አርቃይ በመወርወር ማክሰኞ ህዳር 28/2008 ዓ.ም አዲ-አርቃይ ላይ ከወያኔ መከላከያ ሰራዊትና የሚሊሻ ታጣቂ ኃይል ጋር ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1፡00 ለሶስት ተከታታይ ሰዓታት የዘለቀ ከባድ ውጊያ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የጠላት ጦር በመግደልና በማቁሰል ድልን ተጎናፅፏል፡፡
ሰራዊታችን በጦር ሜዳ ውሎው፣ ከጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት በተቀዳ ወኔ፣ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የህወሓትን መከላከያ ሰራዊትና የሚሊሻ ታጣቂ ኃይል በጦር ሜዳው ላይ በጥይት ቆልቶና አሳሮ አስቀርቶታል፡፡
ፍልሚየው በማግስቱ ረቡዕ ህዳር 29/2008 ዓ.ም ከጥዋቱ 1፡00 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ሰዓታት ማለትም እስከ ረፋዱ አራት ሰአት በዚያው አዲ-አርቃይ ላይ የቀጠለ ሲሆን ፣ ወያኔ ከሌላ ቦታ አጓጉዞ ለጦርነት ያሰለፈውን ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ጀግኞቹ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የነፃነት ፋኖዎች የጠላትን ጦር ድባቅ መትተውታል፡፡
ለነፃነት የሚደረገው ጦርነት አሁንም ቀጥሏል፡፡የወያኔ ባለስልጣናት የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው በተለይ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የሚገኘውን ድንበር የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሰራዊት ለመዝጋት ቢሯሯጡም ድንበር ላይ የተመደበው ወታደር ከወያኔ እየከዳ የነፃነት ትግሉን ከነትጥቁ እየተቀላቀለ ይገኛል፡፡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሰራዊት በተቀዳጀው ድል የአካባቢው ህዝብ ጮቤ እየረገጠ እደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ጀግናው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሰራዊት ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ፣ በህዝብ ድጋፍ ታጅቦ ወደ መሃል አገር እየገሰገሰ ነው፡፡
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
ጃዋር መሃመድን እንደ ጁሌስ ማሌማ? (ከቻላቸው ታደሰ)
ወንድሜ ጃዋር መሃመድ ሆይ! ጥሩ የፖለቲካ ግንዛቤ እንዳለህ መካድ አይቻልም፡፡ የመብት አቀንቃኝም ነህ፡፡ ሆኖም ግን አሁን የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ተማሪዎች ላነሱት ጥያቄ ተከታታይ አጀንዳዎች ስትቀርፅላቸው አላየሁም፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ በመሆንህ (እኔም ስለሆንኩ) የተማሪዎቹን ጥያቄ አመክንዮ በመተንተን፣ የተለያዩ እና ተከታታይ አጀንዳዎችን በማቀበል፣ ለትግላቸው ስትራቴጂ እና ታክቲክ በመቅረፅ ስትረዳቸው አላየሁም፡፡ አንተ እኮ የትግል ስትራቴጂዎች እና አጀንዳዎች ፋብሪካ መሆን ነበረብህ… “Setting the agenda” የሚለው ተወዳጁ የአልጀዚራ ቴሌቪዥን መሪ ቃል ዋና መመሪያህ ይመስለኝ ነበር…
የመጀመሪያውን አጀንዳ (ብዙ የማይስማሙበት ሰዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) በሌላ ወሰብሰብ ወዳለ ሀገራዊ አጀንዳ እየቀየርክ እንካችሁ ትላለህ ብዬ ብጠብቅም አንተ ግን ከወሊሶ እና ጀልዱ የሚደርሱህን ሪፖርቶች ብቻ እየቀመርክ የቁስለኛ ቁጥር እና ፎቶ ብቻ ትለጥፋለህ፡፡ ይህንማ ሌላውም ተራ ሰው ያደርገዋል! አንድ አጀንዳ ብቻ አንጠልጥሎ ትግል የለም፡ ለአንድ ብሄር ብቻ የሚደረግ ትግልም ቢሆን የትም አይደርስም፡፡ የትግሉን አድማስ እና አጀንዳ ማስፋት ከአንተ ይጠበቃል፡፡ (I believe you have a special privilege to seize the momentum in terms of language and social capital so much so that you can contribute in resolving the predicaments of the Ethiopian state and shape a new Ethiopia that would be a better home for all of us) ይህን ካለደረክ ከቀደምቶችህ በምን ልትለይ ነው? እኤአ የ1989ኙ የቻይናው “Tiananmen አደባባይ” ታሪክ እስኪደገም እየጠበክ ነው?
በሀገራችን እስካሁን የተማሪዎች ትግል የህዝብ አጀንዳ እና ትግል የሆነው በ1966 ዓ.ም ብቻ ነው፡፡ እሱም ቢሆን በልሂቃን እንዝህላልነት በከፊል ባክኖ ቀርቷል፡፡ ሀገራችንም እነሆ አርባ ዓመት ሙሉ “ያልተቋጨ አብዮት” (unfinished revolution) ተሸክማ ወገቧ ጎበጠ፡፡ እውነት ግን ለየትኛውም ትውልድ እንዳልተመለሰ ጥያቄ የሚከብደው ሸክም ይኖራል? ሀገሪቱ ብቻ ሳትሆን የእኛ የድህረ አብዮት ትውልድም በሃሳብም በአመለካከትም እየጎበጠ የመጣው የሸክሙ ጫና ሳይሆን አይቀርም፡፡ ባልተመለሱ ጥያቄዎች ላይ ሌላ ሸክም ሲጨመርበት እንዴት አይጎብጥም?
የአሁኑ የተማሪዎች ጥያቄም ስትራቴጂ እና ተከታታይ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ነድፎ የሚያቀብለው ልሂቅ (ልሂቃን) በማጣቱ ብቻ ኪሳራ ሆኖ ሊቀር ነው… ይህ የተማሪዎች እምቢተኝነት ያነገበው ዋና ዓላማ ምንም ይሁን ምን በጥቅሉ ግን ያልተጠበቁ ፍሬዎችን ሊያስገኝ የሚችል ነበር… ይህ ተቃውሞ (protest) ግብታዊ (spontaneous) ቢሆን ኖሮ ልሂቃን (አንተን ጨምሮ) ስትራቴጂ እና አጀንዳ ለመቅረፅ ጊዜ አጥሯቸው ነው ሊባል ይችል ነበር… ይህ ግን ሲፍገመገም የቆየ ነገር ነው… ለጊዜው ይህ የምናየው ነገር protest ነው? ወይስ revolt ነው? ወይስ rebellion ነው? ወይስ uprising? ወይስ… የሚለውን የsemantics ጨዋታ ለጊዜው ልተወው… እሱን እሱን ታላቁ ምሁር ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በኋላ ይነተነትነዋል…
ጃዋር ሆይ! እባክህ ወደ ደቡብ አፍሪካው ወጣት የመብት ታጋይ ጁሌስ ማሌማ ተመልከት፡፡ ከማሌማ ጋር በእድሜ እኩዮች ናችሁ፤ በትምህርት ግን ከማሌማ ብዙ ሳትልቅ አትቀርም፡፡ ጁሌስ ማሌማ እኮ የወደፊቷ ደቡብ አፍሪካ ምን መምሰል እንዳለባት አስቀድሞ በመቅረፅ እና ለደቡብ አፍሪካ ወጣቶች የትግል አቅጣጫ መንደፍ የቻለ ትጉህ ወጣት ነው፡፡ ማሌማ የሚታገለው ለመላ ደቡብ አፍሪካዊያን ነው… ማሌማ የድህረ-ማንዴላ ትውልድ ማንነት መገለጫ ነው…
ጃዋር ሆይ! አንተ የድህረ-ሌንጮ ትውልድ አባላት የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉህ፡፡ የትግልህን ማዕከል በድህረ-1983 ትውልድ ላይ አድርገው… አዛውንቶቹን ልሂቃን (old guards) አንዳንዴ ለምክር ብቻ! የተማሪዎቹ ስልጣኔ እኮ የሚገርም ነው፡፡ በእኛ ጊዜ ከነበረው አንፃር ሳየው ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረግ ረገድ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ተማሪዎች ግሩም ስልጡንነት እየታየባቸው ነው… ይህንን ለሀገራዊ ንቅናቄ አለማዋል ትልቅ ብክነት ነው፡፡ የሞራል ተጠያቂነትም ያስከትላል… አሁን ስለ ተማሪዎቹ ትግል ዕጣ ፋንታ “የቢሆን መላ ምቶች” (scenarios) አስቀምጥ ብትባል ምን ታስቀምጣለህ? መሬት ላይ ጠብ የማይሉ መላ ምቶችን ማስቀመጥ የሚቻለው በአግባቡ ተነድፎ ስራ ላይ እየዋለ ያለ የትግል ስትራቴጂ ሲኖር ብቻ ነው… ያ ደግሞ የለም! ስለዚህ የምታስቀምጣቸው መላ ምቶች አንድ ጉዳዩን በቅርብ ርቀት የሚከታተል ሰው ከሚያስቀምጣቸው መላ ምቶች የሚለዩ አይመስለኝም… እንደዚያ ከሆነ ከመብት ተሟጋችነትና ታጋይነት ይልቅ እንደ እኔው ሁሉ ተራ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ብቻ አድርጌ ላይህ እገደዳለሁ…
ኢትዮጵያ የጁሌስ ማሌማ ያለህ እያለች ነው… ጃዋር ሽፍንፍንህን ጥሰህ እንድትወጣ ምኞቴ ነው… ያ ማለት ግን የብሄር ጥያቄን እርግፍ አድረገህ ተው ማለት አይደለም፡፡ ከውስጥም ከውጭም ብዙ ግፊቶች ቢኖሩበትም (በመጥፎም በጥሩም) የብሄር ማንነት እና በእሱ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ትግል ግን ማመቻመች (pragmatism) እንደሚጠይቅ ሳታውቅ ቀርተህ ነው? እንደ ብሄር ጥያቄ ሆኖ የተጀመረን የመብት ትግል እንደ ተጨባጭ ሁኔታው እያዩ ወደ ሀገራዊ ጥያቄ ማሸጋገር ብልህነት ነው፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ትግልህ የ“ክብ ጉዞ” (circular journey) ይሆንብሃል…
ድሮ ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ትምህርት ወስዶ ነበር፤ መቼም ታሪክ ምፀተኛ ስለሆነ እስኪ አንተም በተራህ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሂደህ ከጁሌስ ማሌማ ጋር ትንሽ ተመካከር… እሱ ልጅ ልዩ የመብት ተሟጋችነት የፖለቲካ ስትራቴጂ የመቅረፅ ተሰጥዖ እንዳለው አልጠራጠርም፡፡ ጭራሽ ሰሞኑን “ማንዴላ የሚባል ሃይማኖት የለኝም” (“I don’t have a religion called Mandela”) ሲል ሰምቼው አስደምሞኛል፡፡ የራስን ማንነት መቅረፅ… ከሽፍንፍኑ መውጣት ማለት እንዲህ ነው… Single-mindedly ማንም ከማይደፍረው የማንዴላ መንፈስ ተላቋል፡፡
ለአንተም ከአንጋፋዎቹ የትግሉ መሪዎች መንፈስ መላቀቅ እነሱን መጥላት ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ላይ የሚታየኝ ምፀት ግን ዶክተር ሌንጮ ለታ ዕድሜው ገፍቶም እንኳ ቀድሞህ ከድሮው የተለየ አጀንዳ ቀርፆ መምጣቱ ነው፡፡ ዝነኛው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሌንጮ ብዙ ቢዘገይም እንኳ ነፍስያውን በደንብ ፈትሾ (soul searching አካሂዶ) መሰረታዊ ለውጥ ማድረጉ ግትር ፖለቲካ በሚታይባት ሀገራችን ፈር ቀዳጅ ሳይሆን አይቀርም… Thumbs up, Dr Lencho የምንለው ወደን አይደለም፡፡ የፖለቲካ ትግል ብዙ ቅያሶች እና የማይተነበዩ ሁኔታዎች (uncharted waters) እንደሚበዛው ቢታወቅም ያልተጠበቀ ነገር ሲመጣ ደግሞ መቀበል ነው… ፈረንጆቹ risk taker የሚሉት መሆኑ ነው… ሌንጮን የሚያስመሰግነው በዚህ ጥልቅ ይሁን አይሁን በማይታወቅ uncharted waters ውስጥ ዘው ብሎ መግባቱ ነው… ይኸው እስካሁን አለ… ማዕበል ጠራርጎ አልወሰደው!
የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስፊልድ ስልጣን ላይ እያለ በሚከተለው አባባሉ ስሙ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡ “There are known knowns. There are things we know we know. There are known unknowns. That is to say we know there are some things we do not know. But there are also unknown unknowns. There are things we don’t know we don’t know.” አባባሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና የሚጠይቀውን ፖለቲካዊ ትግል በደንብ ሳይገልፅ አይቀርም፡፡ እስኪ አንተም ወደ ኦሮምኛ ተርጉመው፤ እኔም ወደ አማርኛ ለመተርጎም እየሞከርኩ ነው፡፡
በሚተነበይ እና በሚታወቅ ጠባብ ሁኔታ ራስን ወሽቆ የተዋጣለት መብት ተሟጋቾች መሪ መሆን ሳይከብድ ይቀራል? ጁኔስ ማሌማ እኮ rsik taker ነው፡፡ አባል የነበረበትን ገዥውን የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግሬስ እያብጠለጠለ “የኢኮኖሚ ነፃነት ታጋዮች” (Economic Freedom Fighters) የተባለ ድርጅት አቋቁሞ ለነባሮቹ የነፃነት ታጋዮች (old guards) የእግር እሳት ሆኖባቸዋል… ይህ ሳይበቃው የማንዴላን መንፈስ መፈታተኑን ተያይዞታል፡፡ ይህ መንገደድ አደጋም ትሩፋትም ሊያመጣለት ይችላል፡፡ ለእኔ ዋናው ነገር ምን መሰለህ? Julius Malema is experimenting with the politics of the post-Mandela South Africa which is visibly in the making. የማሌማ የትግል ዓለም በኩሬ ውሃ (stagnant water) ሊመሰል አይችልም፡፡ የማሌማ ትግል እንደ ወራጅ ጅረት ነው… ልክ በክረምት እየተፎገላ እንደሚፈሰው አዋሽ ወንዝ! ፀጋዬ ገብረ መድህን እንደተቀኘለት አዋሽ! ጁሌስ ማሌማ የማያውቀውን የአዋሽ ወንዝን መንፈስ ተላብሶታል፡፡
አሁን ሰሞኑን አልጀዚራ ሁኔታውን ሲዘግብ የተጠቀመበት ቃና ለማንም አይጠቅምም፡፡ Populist ለሆኑ የመብት ተሟጋቾች በስተቀር ለሀገሪቱም ለትውልዱም አይጠቅምም፡፡ አልጀዚራ ምን ያድርግ? እኳን ለአልጀዚራ በአግባቡ የተቀናበረ ገላጭ እና ኢትዮጵያን ወካይ መልዕክት ማስተላለፍ የሚችል ለተማሪዎቹ አቅጣጫ የሚያሳይ ሰው እንኳ የለም፡፡
(ማስታወሻ፡ ይህን ለመፃፍ በዋነኛነት ያነሳሳኝ በጊዜዬ ከጓደኞቼ ጋር ለተማሪዎች መብት በመታገል ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ነፃ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህብረት በስንት ትግል ካቋቋሙት እና በግንባር ቀደምትነት ከመሩት ውስጥ በመሆኔ… የተማሪዎች ትግል ስለሚያንገበግበኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያኔ አብረውኝ ከነበሩት ውስጥ አንዱ አይበገሬ የመብት ተሟጋች እና ጓደኛዬ ዶክተር አሰግድ ወርቃለማሁ አሁን በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ በእንግሊዘኛ ቃለ ምልልስ የሚያደርግበትን show የሚያዘጋጀው ልጅ ነበር…)
ሰማያዊ ፓርቲ ለተገደሉት እና ጉዳት ለደረሰባቸው አጋርነቱን
• ከመድረክ እና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ወስኗል
ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ ታህሳስ 3/2008 ዓ.ም በካሄደው የብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ከ‹‹ማስተር ፕላኑ›› ጋር በተያያዘ ለተገደሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው የህሊና ፀሎት ያደረገ ሲሆን አጋርነቱን መግለፁንም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ውይይት ያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በተቃወሙት ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው ኢ-ሰብአዊ እርምጃ እና ለሱዳን በሚሰጠው መሬት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊትም ማስተር ፕላኑን በመቃወማቸው በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ለገደሉትና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የህሊና ፀሎት እንደተደረገ ሰብሳቢው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
ማስተር ፕላኑ አርሶ አደሮችን የሚያፈናቅል እና ለመሬት ቅርምት የሚዳርግ መሆኑን በመግለፅ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ለተገደሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን አጋርነት የገለፀው ሰማያዊ ፓርቲ በቀጣይነት በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለና የተደራጀ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ተገልጾአል፡፡ ፓርቲ ከመድረክ ጋር ለመስራት ውይይት መጀመሩን የገለፁት አቶ ይድነቃቸው ከበደ በቀጣይም ከመድረክና ከሌሎች በወቅታዊ ችግሮች ላይ ለመስራት ፈቃደኛ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር እንዲሰራ ብሄራዊ ምክር ቤቱ መወሰኑን ገልፀዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ኀዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ‹‹በገዛ አፈ-ሙዙ መቃብሩን የሚቆፍር የሽንፈትን ጽዋ ይጎነጫል !›› በሚል ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ባሰሙት ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት የወሰደውን ኢ-ሰብአዊ እርምጃ ማውገዙ ይታወሳል፡፡
የታዋቂዋ አርቲስት የማሪቱ ለገሠ ልጅ የቀብር ሥነ ሥርዓት በጅዳ ተፈጸመ !(ነቢዩ ሲራክ)
* “እናቴ ወደ ሀገር ስትገባ አብሬ እገባለሁ ! ” ብላ እንደ ወጣች ቀረች …
የታዋቂዋ አርቲስት የማሪቱ ለገሰ ልጅ ወ/ት ወደሬ ከበደ በጅዳ ተቀበረች ! ሳውዲ ጅዳ የዛሬ ሁለት ሳምንት በአደረባት ህመም ከዚህ አለም በሞት የተለየችው ወ/ት ወደሬ ከበደ ከአሰሪዎቿ ቤት ሁና ህክምናዋን ስትከታተል ቆይታለች ። ደካክማ ከስራ ቦታ አበራ ትኖርባቸው ወደ ነበረበት ቤተሰቦችዋ መጣች ። ” ለምን እስክትደካክሚ ጠበቅሽ ?” ብለው የተደናገጡ ቤተሰቦች ሲያነጋግሯት ወደ ሀገር መግባት እንደምትፈልግ አሳውቃቸው በዚያው ቀን ወደ ሀገር የመግቢያ ሰነድ ለመጠየቅ ወደ ጅዳ ቆንስል አመሩ ። ቤተሰቦችዋ በህመም የተጎሳቆለችውን ወ/ት ወደሬ ከበደን ይዘው ወደ ጅዳ ቆንስል ያመሩት ቤተሰቦች መንገድ ላይ አስደጋጭ ሁኔታ ተፈጠረ ፣ እህት ወደሬ ትንፋሿ አቆመ ፣ ሰውነቷ ቀዘቀዘ … ህዳር የአርቲስት ማሪቱ ለገሠ ልጅ ወ/ት ወደሬ እስከ መጨረሻው አንቀላፋች frown emoticon ህዳር 20 ቀን 2008 ዓም …
ይህን የተረዱ የተጨነቁ ቤተሰቦች በዚያው ቅጽበት በተፈጠረው አስደንጋጭ ሀዘን ግራ ተጋብተው መንገዳቸውን ወደ ጀመሩት የጅዳ ቆንስል አደረጉ … ሬሳውን በመኪና ላይ አስቀምጠው ሬሳ ማስቀመጫ ፈቃድ ለማውጣት የወጡት የወረዱበት ድካም ሀዘንተኞቹን ጎዳቸው … ከሰዓታት እንግልት በኋላ የወደሬ አሰሪዎች ባደረጉላቸው ትብብር ሬሳውን በክብር ማሳረፍ መቻላቸው ተገልጾልኛል። ከዚያም በቀጣይ ቀናት አስፈላጊ የመቅበሪያ ውክል ከቤተሰብ በኩል ከውጭ ጉዳይ አስልከው በሁለት ሳምንት ጊዜ ለቀብር አስፈላጊውን ሁሉ አሟልተው መጨረሳቸውን መረጃውን ያቀበሉኝ የቤተሰቡ አባላት አሳውቀውኛል …
ከወ/ት ወደሬ ከበደ ጋር 11 ልጆቿን ያጣችው ታዋቂዋ የባህል ድምጻዊ ማሪቱ ለገሰ አሁን የቀራት አብዱ የሚባል ልጇ ሲሆን ዛሬ የቀብር ሥነ ሥርዓቷ የተከዎነው ወ/ት ወደሬ የአብዱ ታላቅ እህቱ እንደ ነበረች ተጠቁሟል ። እህት ወደሬ ከአርቲስት እናቷ ከማሪቱ ለገሠ ጋር ትኖር የነበረ ሲሆን የዛሬ 20 ገደማ ድምጸ አርቲስት ማሪቱ ለገሠ ወደ አሜሪካ ስትሔድ እሷም ወደ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ መምጣቷን በቅርብ የሚያውቋት አጫውተውኛል ። እኒሁ የቤተሰብ አባላትና የቅርብ ወዳጆች በማከልም ” ወደሬ ለኑሮዋ የሚጎላት ነገር ባይኖርም እናቴ ወደ ሀገር ስትገባ አብሬ እገባለሁ ! ” ብላ ስትጠባበቅ ባደረባት የስኳር ህመም እንደወጣች በሞት ከዚህ አለም መለየቷን በሀዘን በተጎዳ ስሜት በዝርዝር አስተድተውኛል !
የተወዳጇ ድምጸ መረዋ አቀንቃኝ የማሪቱ ለገሠ ልጅ ወ/ት ወደሬ ከበደ የቀብር ሥነ ሥርዓት ታህሣሥ 3 ቀን 2008 ዓም ከምሽቱ የኢሻ ጸሎት በኋላ ልዩ ስሙ ባብ ሸሪፍ በሚገኝ ቢን ማዕሩፍ በተባለ መስጊድ የቅርብ ወዳጅ ዘመዶችና አብሮ አደጎቿ በተገኙበት ተፈጽሟል !
የተወዳጇ ድምጸ መረዋ አቀንቃኝ ለማሪቱ ለገሠ ፣ ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማድና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ ! የሟችንም ነፍስ ይማር !
ታህሣሥ 4 ቀን 2008 ዓም
( ፎቶው የተወዳጇ ድምጸ መረዋ አቀንቃኝ የማሪቱ ለገሠ ነው)
አትሌቶች ተቃውሞ ያነሳሉ በሚል ፍርሃት የኦሮሚያ ክለቦች ውድድር ተሰረዘ።
በመላው ኦሮሚያ በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት 3ሺህ አትሌቶች ከተለያዩ ኦሮሚያ ክለቦች የሚካፈሉበት ውድድር በአሰላ ሊካሄድ አትሌቶች አሰላ ከገቡ በኃላ ተሰረዘ።
ዛሬ ይጀመር የነበረው ውድድር ላይ አትሌቶቹ በመላው ኦሮሚያ መንግስት ልዩ ጦር አዝምቶ ወገኖቻችንን እየገደለና እያሰረ መሆኑን በመቃወም በመክፈቻ ሰነስርዓት ላይ ጥቁር ለብሰው ሊገቡ እንደሆነ ስለተደረሰበት ውድድሩ ሊሰረዝ ችሏል።የቃልኪዳን ቲዩብ ምንጮች እንደገለጹት የአሰላ ህዝብ በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሞ ተቃውሞውን ይገልጻል በሚል ፍርሃት እና ተቃውሞው በአትሌቶቹ መደገፉ ለህዝብ ተጨማሪ መነሳሳት ይሆናል በሚል ከፌደራል በቀጥታ በመጣ ትእዛዝ ሊሰረዝ መቻሉን ገልጸውልናል።
አትሌቶቹ ሰሞኑን በልምምድ ሜዳዎች ላይ”መግደል ይቁም፣ገበሬው አባታችንን የሚያፈናቅል ማስተር ፕላን እናወግዛለን፣የ6ብር ግምት ለገበሬው ሰጥቶ በሚሊዮን የሚሸጥበት የመሬት ዝርፍያ ይቁም”የሚሉ ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
አንድ ወር ሊሞላው ሁለት ቀን የቀራው በመላው ኦሮሚያ በተነሳው ተቃውሞ መንግስት የኅይል እርምጃ መውሰድና መግደል የቀጠለ ሲሆን በትላንትናው ቀን ብቻ 25ሰዎች ተገድለዋል።እስካሁን ከ50በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የኦሮሚያ ፖሊሶች ወገኔን አልገልም በማለታቸው ልዩ ኮማንድ ፖስት በፌድራል መንግስት ተዋቅሮ ድምጹን እያሰማ ያለውን ህዝብ ከመግደል የሚጀምር እርምጃ ሊወስዱ ከተለያዩ የጦር ካንፖች ወደህዝቡ ተልኳል።
ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ እየተደረገበት ያለው ህዝብ መሳርያ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ተናንቆ በ152ቦታዎች ድምጹን እያሰማ ነው።