በኦሮሚያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ዛሬ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። በዛሬው እለት በአዳማ ዩኒቨርሲቲና በምስራቅ ሃረርጌ የተቃውሞ ሰልፎች ነበሩ ያለው ቪኦኤ እንደሰሞኑ ሁሉ የአድማ በታኝን የመከላከያ ኃይሎች ሰልፈኞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ሲል ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከደረሰው የቦምብ ፍንዳታና ግድያ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንደወጡ ገልጿል።ዛሬ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በብዛት የትምህት ቤት ቅጥር ጊቢውን ለቀውእየወጡ መሆናቸውን የገለጸው ቪኦኤ ባለፈው ሳምንት በቦምብ ፍንዳታ የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ካለፈ በኻላ የተማሪዎች መኝታ ክፍሎች ተቃጥለዋል ሌሎች ሁለት ተማሪዎች ደግሞ ተገድለው አስከሬናቸው መታጠቢያ ቤት ውስጥ እንደተገኘ ሌላ አንድ ተማሪ አሰከሬን ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ አቅራቢያ በሚገኝ ደን ዉስጥ እንደተገኘ ዘግቧል።
ዛሬ ማለዳ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለውን መቃወማቸውን ቪኦኤ ከስፍራው ያነጋገረው ተማሪ አረጋግጧል “በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች የኦሮሞ ተማሪዎችን ከሌሎች ተማሪዎች እየለዩ ወደ ቅጥር ጊቢው እንደሚመልሱ ” የገለጸው ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ተማሪ “ጥቃት እንዳይደርስብን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን” ብሏል።” ዩኒቨርሲቲው የጦር ሰፈር እንጂ የትምህርት ተቋም እንደማይመስል ጠቅሶ ቁጥጥር ስር ስለዋሉ ተማሪዎችም ስም ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምስራቅ ሃረርጌ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ከጥዋት ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ሰልፈኞቹ ከአካባቢው ገጠሮች በሶስት አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ እንደገቡ ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቀው የሰልፉ ተካፋይ ለቪኦኤ ተናግረዋል። የኦሮሚያ ፓሊስ ሰልፉን እንዲያቆሙ ቢያዝም ሕዝቡ ባላማቆሙ ተጨማሪ ኃይል ወደ ከተማዋ መግባቱን ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁ የአይን እማኝ ገልጸዋል።
“ሰልፉ ትንሽ እንደቆየ አጋአዚ የሚባለዉን ኃይል ጨምረው በማምጣት ተኩስ ከፈቱ። ሰልፉም ተበተነ። ነጋዴዎችና ሌላው ነዋሪዎች ህዝብ ከሶስት እቅጣጫ ወጥቶ ስለነበር ህዝቡ ብዙ ነበር ። ሕዝቡ በሩን ዝግቶ ነው የወጣው” ብለዋል።
አቶ አህመድ ሙሚ የተባሉ የቆቦ ከተማ ነዋሪ በሰልፉ ላይ አናታቸውን በዱላ ተመተዉ መቁሰላቸውን የገለጸው ዜናው የመንግስት ታጣቂዎች ጥይት ወደ ሰማይ እየተኮሱ ሰልፈኛውን እንደበተኑ ሰልፈኞች እንደነገሩት ቪኦኤ ገልጿል። ተጨማሪ የፌደራል ኃይል ወደ ከተማዋ እየገባና የከተማዋ ፖሊሶች ደግሞ ከቤት እቤት በመዘዋወር የሰልፉን ተካፋዮች እያደኑ መሆኑ በነዋሪዎቹ ተገልጿል። የቆቦ ከተማ ሱቆችና ምግብ ቤቶች ዝግ ናቸው ከተማዋም ከሚዘዋዋሩባት የጸጥታ ሃይሎቹ በስተቀር ጭር ብላለች ተብሏል።የቪኦኤን ዘገባ ያዳምጡ።
↧
ዛሬ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ እና በምስራቅ ሃረርጌ የተቃውሞ ሰልፎ ተደረገ – VOA Amharic
↧